ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጠናክሮ ቀጥሏል

 አዲስ አበባ፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  ተጠናክሮ መቀጠሉን የከተማዋ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የሸገር ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳጀኔ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማዋ በተያዘው የክረምት ወራት በ 5 ሺ 540 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

በክረምቱ ወራት ለሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ18 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑና የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ማዘጋጀት ተችሏል ነው ያሉት።

ለተከላ የተዘጋጁት ችግኞች ለምግብነት፣ ለከተማ ውበት እና የደን ሽፋንን ጨምሮ ለሌሎች አገልግሎቶች እንደሚውሉም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከ 4 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ ከ12 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ቀሪዎቹን ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን በተካሔደው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ 580 ሺህ ዜጎችና  የተለያዩ ማህበራት ተሳትፎ ማድረጋቸውንም አቶ ዳጀኔ ገልጸዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተተከሉ ያሉ ችግኞች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸውም ጠቁመዋል።

በከተማዋ እስካሁን ከተተከሉት ችግኞች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት አትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸው ተገልጿል።

በሸገር ከተማ እየተከናወነ ያለው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአፈር ለምነትን በመጨመርና ምንጮችን በማጎልበት የአርሶ አደሩን ምርት እና ምርታማነት እያሳደገ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥም ቀደም ሲል በአንድ ወቅት ብቻ በዝናብ ጥገኝነት ይካሔድ የነበረውን የምርት ስራ በመቀየር በበጋውም ወራት የእርሻ ስራ እንዲካሔድ በማድረግ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት።

መርሃ ግብሩ የከተማዋን ውበት በመጠበቅ ረገድም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች ከተማዋ የነበራትን 11 በመቶ የደን ሽፋን ከ 21 ነጥብ9 በመቶ በላይ ለማሳደግ አስችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም