49ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
49ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 21/2018(ኢዜአ)፦ 49ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ከዛሬ ጀምሮ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል።
የምክር ቤቱ ስብስባ “ ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚለው የ2026 የህብረቱ ዓመታዊ መሪ ሀሳብ አማካኝነት ይከናወናል።
በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አዘጋጅነት በሚካሄደው የሁለት ቀናት ስብሰባ ላይ የህብረት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ቁልፍ አጀንዳዎች እና የአፍሪካን አህጉራዊ ትስሰር ማፋጠን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ።
በስብስባው ላይ ሚኒስትሮቹ የአጀንዳ 2063 አፈፃፀም የሚከታተለውን ኮሚቴ ሪፖርት እንዲሁም የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና በአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ወቅት ያሉ ስምምነቶችና የአሰራር ማዕቀፎች ያሉበትን የትግበራ ደረጃ ይገመግማሉ።
በተጨማሪም የ2026ቱን የህብረቱን የዓመቱ መሪ ሀሳብ የእስካአሁን የአፈጻጸም ሂደት ላይ እንደሚወያዩም ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይህ የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ የፖሊሲ ትብብር ለማጠናከር እና የአህጉሪቱን አጀንዳዎች አፈፃፀም ለማፋጠን የአፍሪካ ህብረት እያደረገ ያለው ጥረት አካል ነው።
ስብሰባው እ.አ.አ. በ2017 በህብረቱ አባል ሀገራትና መንግስታት መሪዎች የፀደቀውን ተቋማዊ ማሻሻያ መነሻ ያደረገ ነው።
ማሻሻያው በህብረቱ፣ በክፍለ-አህጉራዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች፣ በክፍለ-አህጉራዊ አሰራሮች እና በአባል ሀገራት መካከል ያለውን የኃላፊነት ክፍፍል በግልጽ ያስቀመጠ ነው።
በተጨማሪም ቀደም ሲል በየዓመቱ በሰኔ እና በሐምሌ ወር ይደረግ የነበረውን የመሪዎች ስብሰባ በማስቀረት፣ በምትኩ ህብረቱ ከክፍለ-አህጉራዊ ተቋማት ጋር አብሮ የሚሰራባቸውን አዳዲስ የጋራ ስብሰባዎች እንዲተካ አስችሏል።
ከዚህ ስብሰባ የሚገኙ ውጤቶች አህጉራዊ ዘላቂ ልማትን፣ ትስስር እና ብልፅግናን እውን ለማድረግ የተቀረፀውን የአፍሪካ ህብረት የረጅም ጊዜ መሪ እቅድ (አጀንዳ 2063) ስኬታማ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው የህብረቱ መረጃ ያመለክታል።
49ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ እስከ ነገ ይቆያል።