ቀጥታ፡

በቀድሞ የሲዳማ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ የጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ተላለፈ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ) ፦ የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀድሞ የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ጢሞቴዎስ እና በቀድሞው የፖሊስ ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ ላይ የጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

የክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ በማስደገፍ ለክልሉ ፍትህ ቢሮ ያቀረበውን የምርመራ መዝገብ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ተመልክቷል።

ተከሳሾቹ ሥልጣንን ያለግባብ በመገልገል "የሲዳማ ነፃነት ሠራዊት" የተባለ ታጣቂ ቡድን በማደራጀት ተደራራቢ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውንም በማረጋገጥ ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

በዚህም መሠረትም ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ አቶ ዓለማየሁ ጢሞቲዎስ በ10 ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራት እና በ4 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ወስኗል።

ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ሽመልስ ቶማስ ደግሞ በ1 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እና በ1 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ውሳኔ ማስተላለፉን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም