ቀጥታ፡

 ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ በክረምት ወቅት የሚሰሩ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎችን ገመገሙ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ ማምሻውን ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር በክረምት ወቅት የሚሰሩ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎች፥ የቤት ግንባታ፣የጎርፍ አደጋን መከላከል ፥ የፅዳት ስራዎች፥ የአረንጓዴ አሻራ፥ ማዕድ ማጋራት፥ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ፥ ደም ልገሳ፥ ተረጅነትና ድህነት ቅነሳ  ስራዎች አፈፃፀምን መገምገማቸውን አስታውቀዋል።

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሁሉም መስክ ውጤታማ ተግባራት እየተፈፀሙ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል። ሆኖም በክፍለ ከተሞች እና በተቋማት መካከል የአፈፃፀም ልዩነቶች እንደሚታዩም ገልጸዋል።


 

በቀጣይም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በቅንጅት መመራት የሚገባቸው፡-

👉የጀመርናቸዉን የቤቶች ግንባታን ማፉጠን፣

👉ዲቾችን ማፅዳት እንዲሁም አዳዲስ ዲቾችን መገንባት

👉ከፍተኛ ሀብት ፈሶባቸው የለሙ ቦታዎች መንከባከብ ፅዳታቸውን መጠበቅ

👉አጠቃላይ የከተማ ፅዳት ባህል እንዲሆን መስራት

👉 በግንባታ ምክንያት በተረፈ ምርቶች መንገዶችን የሚያበላሹ፥ ዲቾችን የሚዘጉ አካላት በአፋጣኝ ችግሩን እንዲያርሙ ተጠያቂም እንዲሆኑ ማድረግ

👉 በአረንጓዴ አሻራ የጀመርነው ውጤታማ ስራ ለጥራቱም ትኩረት መስጠት እንዲሁም የችግኝ ተከላ ስራ በአጠረ ጊዜ እና ከእቅድ በላይ ማሳካት

👉 የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሁሉም ዜጋ ባህል እንዲያደርገዉ የማስቻል ስራ መስራት

👉 ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በልዩ ትኩረት መስራት

👉 የጎልማሶች ትምህርት ማጠናከር እንዲሁም  ከተረጅነት ለመሸጋገር የተጀመሩ የሰብዓዊ ስራዎች ለመተግበር መጋዘኖች በጥራት የተገነቡ ቢሆንም ቀጣይ ስራ የሚሆነው በቂ የሰብዓዊ ድጋፍ ቁሶች እንዲኖራቸው ማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ሁሉም አመራር በጥብቅ የሚፈፅማቸው ናቸው ሲሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም