ቀጥታ፡

የሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2018(ኢዜአ)፦ የሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲልቪ ባይፖ ቲሞን እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አብዲሳላም አብዲ አሊ በ49ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።

 


 

በ49ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ የሚሳተፉ ከተለያዩ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የተውጣጡ የልዑካን ቡድኖች ከትናንት ጀምሮ አዲስ አበባ እየገቡ ነው።

በዚህም መሰረት የሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲልቪ ባይፖ ቲሞን እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አብዲሳላም አብዲ አሊ በስብሰባው ለመሳተፍ ምሽቱን አዲስ አበባ ገብተዋል።

ሚኒስትሮቹ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል መላኩ በዳዳ አቀባበል አድርገውላቸዋል።


 

49ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ "የአፍሪካን አጀንዳ 2063 ለማሳካት ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓት ማንበር" በሚል መሪ ሀሳብ ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ በአፍሪካ ሕብረት ዋና መሥሪያ ቤት ይካሄዳል።

በስብሰባው የአፍሪካ ሕብረት የ2026 ዓመታዊ መሪ ሀሳብ አፈጻጸምና የትግበራ ሂደትን በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት ላይ በጥልቀት ውይይት ይደረጋል።

የአፍሪካ ሕብረት ስምምነቶች በቅልጥፍና እንዲጸድቁና ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩ በሚያስችሉ ጉዳዮች፣ እንዲሁም የአጀንዳ 2063 ትግበራን በተመለከተ በኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት ላይ የምክክር መድረክ የሚካሄድ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም