ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ይበልጥ ከማጠናከር ባሻገር ትልቅ የልማት አቅም እየሆነ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ይበልጥ ከማጠናከር ባሻገር ትልቅ የልማት አቅም እየሆነ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ)፦ ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ይበልጥ ከማጠናከር ባሻገር ትልቅ የልማት አቅም እየሆነ መምጣቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
የ2018 ዓ.ም የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል።
ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፤ ሀገራዊ የበጎ ፈቃድ ንቅናቄ ወጣቶች ከራሳቸው አካባቢ በመውጣት ሌሎች ማህበረሰቦችን እንዲያውቁ፣ የጋራ ሀገራዊ ስሜትን እንዲያጎለብቱና የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን እንዲያጠናክሩ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
ለሶስት ሳምንታት በቆየው መርሃ ግብር ወጣት በጎ ፈቃደኞች በአራቱም አቅጣጫዎች በመንቀሳቀስ የተለያዩ ሀገራዊ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን አከናውነዋል።
በዚህም የአካባቢ ጥበቃ፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የማህበረሰብ ድጋፍና ሌሎች ማህበራዊ ተግባራትን በማከናወን ለህዝብ ተጠቃሚነት አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ወጣቶቹ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ድልድዮች በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች የመረዳዳትና የመተሳሰብ መንፈስን ማጠናከራቸውን ገልጸዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የወጣቶችን ጉልበት፣ እውቀትና ችሎታ በመጠቀም በመንግስትና በማህበረሰብ ያልተሸፈኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያግዝ ሀገራዊ ንቅናቄ መሆኑንም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በሀገራዊ ምክክርና በጋራ መግባባት ሂደት ላይ በምትገኝበት ወቅት የወጣቶች ተሳትፎ የሰላምና የአንድነት ግንባታን ለማጠናከር ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ይበልጥ ከማጠናከር ባሻገር ትልቅ የልማት አቅም እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
ተሳታፊ ወጣቶች በበኩላቸው፤ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሩ ሀገራቸውን በተሻለ ለማወቅና የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎችን እውነተኛ ገጽታ ለመረዳት ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በተለይም ለአረጋውያን፣ ለአቅመ ደካሞችና ድጋፍ ለሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች ያበረከቷቸው አገልግሎቶች ትልቅ እፎይታ እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል።
በመድረኩ ለወጣት በጎ ፈቃደኞች፣ ለክልል አመራር አባላት፣ ለጤና ቡድኖች፣ ለመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ለመርሃ ግብሩ ስኬት ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና ቀርቧል።