በኢትዮጵያ ዋናው የምክክር ጉባኤ ለወጣቶች የምትመች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተመካከርን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዋናው የምክክር ጉባኤ ለወጣቶች የምትመች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተመካከርን ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዋናው የምክክር ጉባኤ ለወጣቶች የምትመች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተመካከሩ መሆናቸውን ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተመካካሪ ወጣቶች ገለጹ።
ተመካካሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ከጠቅላላ መድረኮች እስከ ንዑሳን የምክክር ቡድኖች ድረስ የተካሄዱት ውይይቶች ሁሉም ተሳታፊዎች በሚገባቸው ቋንቋ ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲያቀርቡ ዕድል ፈጥሯ።
ይህም በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባትን ለማጠናከር ወሳኝ ዕድል የፈጠረ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጣው ተመካካሪ ወጣት አደም ሳሌ እንደገለጸው፤ የምክክሩ ሂደት ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሌሎች የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በስፋት ያሳተፈ አካታች መድረክ ነው።
በምክክሩ የተለያዩ አስተያየቶችና ሃሳቦች ቢቀርቡም፣ በአብዛኛዎቹ የሀገር ግንባታ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እየተፈጠረ እንደሚገኝ ገልጿል።
ይህም ለረጅም ዓመታት ሳይፈቱ የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግሯል።
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመጣችው ተመካካሪ ወጣት ሊዲያ ኬሮ በበኩሏ፣ ምክክሩ አካታች በሆነ መልኩ በማሳተፍ ልዩነቶችን ወደ መግባባት እየቀየረ መሆኑን ገልጻለች።
የአሁኑ ትውልድ በምክክሩ ያሳየው ተሳትፎና መስዋዕትነት ለሚቀጥለው ትውልድ የተሻለችና የተረጋጋች ኢትዮጵያ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ የሚጥል ታሪካዊ እርምጃ ነው ብላለች።
ከጋምቤላ ክልል የመጣው ተመካካሪ ወጣት ቾል ፑግ በበኩሉ፣ የምክክሩ ሂደት ከመጀመሪያው ጀምሮ በተደራጀና በአካታች መልኩ መካሄዱንና፣ የተሳታፊዎች የጋራ ውይይት ለሀገር ግንባታ የጋራ ኃላፊነትን ለማጎልበት ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጿል።
ችግሮችን በመወያየትና የጋራ መፍትሔ በማፈላለግ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን እንደሚቻልም ነው የተናገረው።
ከድሬዳዋ የመጣው ተመካካሪ ወጣት አሕመድ ሁሴን በበኩሉ፣ በሀገራዊ ምክክሩ መሳተፉ የሀገሪቱን ችግሮች በጋራ ለይቶ በመወያየት ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ በሚደረገው ታሪካዊ ጥረት አካል ነው ብሏል።
ችግሮቻችንን በጋራ ለይተን በመወያየት ተግባራዊ መፍትሔ የሚያስቀምጥ ውጤታማ ምክክር እየተደረገ በመሆኑ ጥሩ ውጤት ይመጣል ሲል ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የቆዩ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት፣ የጋራ ራዕይ ለመገንባት፣ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለማጠናከርና ለቀጣይ ትውልድ የተረጋጋች፣ የተባበረችና ሰላማዊት ኢትዮጵያን ለማሸጋገር ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስተያየት የሰጡት ተመካካሪች ገልጸዋል።