ቱሪዝም - የጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ትንሳኤ በኢትዮጵያ!! - ኢዜአ አማርኛ
ቱሪዝም - የጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ትንሳኤ በኢትዮጵያ!!
መግቢያ፡- ኢትዮጵያ የሰው ልጅ ሥልጣኔ መነሻ፣ የታሪክ መዝገብና የቱባ ባህል ሀብት ካስማ ምድር መሆኗ የአደባባይ ሃቅ ነው። የሺህ ዓመታት ታሪኮች፣ በዘመናት የተገነቡ ዕድሜ ጠገብ የሕንፃ አሻራዎች፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ ባህላዊ እሴቶችና በዓላት ኢትዮጵያን በዓለም የቱሪዝም ካርታ ላይ ልዩ ስፍራ የሚያስይዙ መለያ ምልከቶቿ ናቸው።
እንደ የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሐውልቶች፣ የአልነጃሺ መስጂድ፣ የሐረር ጀጎል እና የጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ያሉ ታሪካዊ ቅርሶች የጥንታዊ ሥልጣኔ፣ የሃይማኖታዊ ትውፊትና የአርክቴክቸር ብልጽግና ሕያው ምስክሮች ናቸው። በተጨማሪም መስቀል፣ ጥምቀት፣ የገዳ ሥርዓት፣ አሸንዳ/አሸንድዬ፣ ኢሬቻ፣ ፊቼ ጨምበላላ እና ጊፋታ የመሳሰሉ የአደባባይ በዓላትም ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሳቡ የማይዳሰሱ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች የሚያንጸባርቁ የኢትዮጵያ ውድ ሃብቶች ናቸው።
እነኝህ ታሪካዊና ባህላዊ ሃብቶች በዓለም አቀፍ ዕውቅናም የተቸራቸው ናቸው። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 16 የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቿን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ማስመዝገብ ችላለች። በቅርቡ የተመዘገቡት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር እና የሐረር ሸዋል ኢድ ኢትዮጵያ ለዓለም ህዝብ ያበረከተቻቸው አዳዲስ የመስህብ ትሩፋቶች ናቸው። እነዚህ ቅርሶች የኢትዮጵያን ገጽታ በዓለም ላይ ከማጉላት ባሻገር በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን በመሳብ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መነቃቃት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በብዝኅ ተፈጥሮ፣ ታሪክና ባህል የታደለች ሀገር ብትሆንም ለረጅም ጊዜ እነዚህን ዕምቅ ሃብቶች በዘመናዊ የቱሪዝም አቀራረብ ለማልማት፣ ለዓለም አቀፍ ገበያ በብቃት ለማስተዋወቅና ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚ ጥቅም ለመቀየር የሚገባውን ያህል ትኩረት ሳይሰጣቸው ቆይቷል። በመሆኑም የቱሪዝም ዘርፍ የሀገሪቱን እውነተኛ አቅም በሚመጥን ደረጃ መጠቀም ሳይቻል ቆይቷል።
በሀገራዊ ለውጡ ማግስት በኢትዮጵያ በተተገበረው ከአምስቱ የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ማሻሻዮች መካከል አንዱ አምድ እንዲሆን በመደረጉ ልዩ ትኩረት አግኝቷል። ይህም ዘርፉ ከተለምዷዊ አካሄድ ወጥቶ ወደ ዘመናዊ ልማት፣ ወደ ከፍተኛ ተወዳዳሪነትና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚሸጋገርበትን መሰረት ጥሏል።
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተተገበሩት "የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክቶች ለቱሪዝም ዘርፉ ለውጥ ወሳኝ ምዕራፍ ፈጥረዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች በተፈጥሮ፣ በታሪክና በባህል የታደሉ ስፍራዎችን በዘመናዊ መንገድ በማልማት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች ማራኪ መዳረሻዎችን መፍጠር ችለዋል። በዚህም የጎብኚዎች ፍሰት ጨምሯል፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝት አድጓል፣ የየአካባቢዎቹ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ተነቃቅተዋል፣ የኢትዮጵያም የቱሪዝም ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ መልክ እያገኘ መጥቷል። ዛሬ ቱሪዝም ለኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ማረጋገጫ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ምንጭ፣ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እና የሀገር ገጽታ ግንባታ ማጎልበቻ ዋና ሞተር በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
ኢትዮጵያ፤ በአፍሪካ ቀዳሚ የዓለም ቅርሶች ማዕከል
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከ16 በላይ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ያስመዘገበች በአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ናት። ከሚዳሰሱት ቅርሶች መካከል የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የፋሲል ግቢና የጎንደር ቤተ መንግስት፣ የአክሱም ሐውልቶች፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ የታችኛው ኦሞና የአዋሽ ሸለቆዎች፣ የሐረር ጁገል ግንብ እንዲሁም የባሌና የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች ይገኙበታል። ከማይዳሰሱት ቅርሶች ደግሞ የመስቀል ደመራ በዓል፣ የጥምቀት በዓል፣ የፊቼ ጨምበላላና የገዳ ሥርዓት ተጠቃሽ ናቸው።
ለቱሪዝም ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት እነዚህን ዓለም አቀፍ ቅርሶች በተሻለ ሁኔታ የመጠበቅና የማደስ ሥራዎች የሚሰሩበትን ዕድል ፈጥሯል። በተመሳሳይም አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ኢትዮጵያን ይበልጥ ተወዳዳሪና ማራኪ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ የሚያስችል ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
ሶስቱ ሜጋ ፕሮጀክቶች
- ገበታ ለሸገር - የአዲስ አበባን ገጽታ የቀየረ የለውጥ ጥንስስ!!
የገበታ ለሸገር መርሃ ግብር የአዲስ አበባን የከተማ ገጽታ በመቀየር የቱሪዝም ስበት ማዕከልነቷን ያጎለበተ የለውጥ ምዕራፍ ነው። በመርሃ ግብሩ የተገነቡት የእንጦጦ፣ የአንድነትና የወዳጅነት ፓርኮች፣ የሳይንስ ሙዚየምና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከተማዋን ከዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ ባሻገር ዓለምአቀፍ የኮንፍረንስ ቱሪዝምና የመዝናኛ ጉብኝት ማዕከል እንድትሆን መሠረት ጥለዋል።
ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞ የተተገበሩት የከተማ ኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ለበርካታ ዓመታት ችላ የተባሉ ስፍራዎችን ወደ አረንጓዴ፣ ዘመናዊ እና ለሁሉም ተደራሽ የመዝናኛ ከባቢነት ቀይረዋል። ይህም ከተማዋን ለጎብኚዎች ይበልጥ ማራኪ ከማድረጉ በተጨማሪ ለነዋሪዎች ጤናማ፣ ንጹህና ምቹ የከተማ ምኅዳር መፍጠር አስችሏል።
ገበታ ለሸገር የአዲስ አበባን የከተማ ውበት በማሳደግ፣ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋትና የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን በማበራከት የቱሪዝም ዕድገትን ያፋጠነ ብቻ ሳይሆን፣ የነዋሪዎችን የኑሮ ጥራት ያሻሻለና የዘመናዊ ከተማ ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስኬታማ ፕሮጀክት ነው።
- ገበታ ለሀገር - ከገበታ ለሸገር የተቀዳ የሀገር በረከት!!
ገበታ ለሀገር መርሃ ግብር በገበታ ለሸገር የተጀመረውን የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ወደ መላው ሀገር በማስፋት፣ በየክልሉ የሚገኙ ዕምቅ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ሃብቶችን ወደ ዘመናዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች የቀየረ ትልቅ የልማት ፕሮጀክት ነው።
በዚህ ማዕቀፍ የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም፣ የጎርጎራ፣ የኮይሻና ሌሎች መሰል ፕሮጀክቶች በመገንባታቸው የክልሎችን የቱሪዝም አቅም በእጅጉ በማሳደግ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች አዳዲስና ማራኪ የጉብኝት መዳረሻዎችን ፈጥረዋል።
በተመሳሳይም ፕሮጀክቶቹ በክልሎች መካከል ፍትሐዊ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ሥርጭት እንዲፈጠር በማድረግ፣ የመንገድ፣ የመስተንግዶ፣ የመዝናኛና ሌሎች ዘመናዊ አገልግሎቶችን የሚሰጡ መሰረተ ልማቶች በስፋት እንዲገነቡ አስችለዋል።
ይህም የቱሪዝም ጥቅም በተወሰኑ ከተሞች ብቻ እንዳይገደብ በማድረግ፣ የአካባቢ ኢኮኖሚን በማነቃቃት፣ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠርና የክልሎችን የልማት ተጠቃሚነት በማሳደግ የቱሪዝም ዕድገትን ወደ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ የቀየረ ውጤታማ ፕሮጀክት ሆኗል።
- ገበታ ለትውልድ - የቱሪዝም ልማትን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ያሸጋገረ የአገልግሎት ዘርፍ እመርታ!!
ገበታ ለትውልድ መርሃ ግብር በገበታ ለሸገርና ገበታ ለሀገር የተጀመረውን የቱሪዝም ልማት በማስቀጠል፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን በዘላቂነት ከመጠበቅ ጋር በማጣጣም ዘመናዊ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማት ያስቻለ አዲስ የልማት ምዕራፍ ነው። መርሃ ግብሩ የቱሪዝም ልማትን ከኢኮኖሚ ዕድገት ባሻገር ለትውልድ የሚተርፍ ሃብት የመጠበቅ እሳቤ ጋር አሰናስሎታል።
በዚህ ማዕቀፍ በቅርቡ የተመረቀው የአርባ ምንጭ ኮንፍረንስ ሪዞርትን ጨምሮ፣ የሸበሌ፣ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርቶችና የሀሮ ደንዲ ኢኮ ሎጅ ተጠናቀው ወደ ሥራ ገብተዋል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተገነቡና እየተገነቡ የሚገኙ ሌሎች የቱሪስት መዳረሻ የልማት ሥራዎችም ዘርፉን በማነቃቃት ከፍተኛ አቅም ፈጥረዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎች በማስፋፋት፣ አገልግሎትን ወደ ዓለምአቀፍ ደረጃ በማሳደግና የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቆይታ በማራዘም በኩል ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው። በተመሳሳይም ለአካባቢያዊ የኢኮኖሚ መነቃቃት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲሁም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ በማሳለጥም ገንቢ ሚና እየተወጡ ይገኛል።
የኮሪደር ልማትና አዳዲስ የቱሪዝም ትስስሮች
በኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ተጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እየተስፋፋ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ውበት እያፈካ ይገኛል። በዚህም የከተሞችን መሠረተ ልማት፣ የአረንጓዴ ስፍራን፣ የመዝናኛና የእግረኛ መንገዶችን በስፋት በማልማት ለነዋሪዎችም ሆነ ለጎብኚዎች ምቹና ማራኪ የከተማ ምኅዳር ፈጥሯል። ይህ ልማት የከተሞችን ውበት ከማሳደግ ባለፈ፣ የቱሪዝም መሠረተ ልማትን በማጠናከር፣ የጎብኚዎችን ቆይታ በማራዘምና የአካባቢውን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ዘርፉን ወደ ከፍተኛ የዕድገት ምዕራፍ አሸጋግሯል።
- የኮንፍረንስ ቱሪዝም (MICE)
የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን ውብ፣ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ከተማ በማድረግ፣ የአፍሪካ ኅብረትና የበርካታ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ተቋማት መቀመጫ የሆነችውን ከተማ ወደ ቀዳሚ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል ቀይሯታል። አዲስ ዓለም ኮንቬንሽን ማዕከል፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የሳይንስ ሙዚየምና ሌሎች ዘመናዊ መዳረሻዎች በአንድ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ተቋማትን በማፍራት ከተማዋን ለሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች፣ ኤግዚቢሽኖችና ትላልቅ የንግድ መድረኮች ተመራጭ አድርጓታል።
ለአብነትም የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፣ የአፍሪካ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS) እና መሰል ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮችን በብቃት ማስተናገድ ተችሏል። በተለይም የአፍሪካ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያላቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች ለዓለም እንዲያስተዋውቁ ምቹ መድረክ ፈጥሯል። ይህም የሀገሪቱን ዓለምአቀፍ ገጽታ ከማጎልበት ባለፈ የቱሪዝም ማስተዋወቅን በዲጂታል ዘመን ከፍ ወዳለ ደረጃ አሸጋግሮታል።
- የስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም
የስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም መርሃ ግብርም የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመጠቀም በአዲስ አበባ የሚያልፉ ትራንዚት መንገደኞችን ከመሸጋገሪያነት ብቻ ወደ ጎብኚነት ለመቀየር አስፈላጊ ዕድል ፈጥሯል። በዚህም መዲናዋን ከቱሪስት መሸጋገሪያነት ወደ ቱሪዝም ማዕከልነት ቀይሯታል። በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማትም ውብና ማራኪ የከተሜነት ገጽታን በመፍጠር፣ መንገደኞች በቆይታቸው የተለያዩ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ዘመናዊ መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ አስችሏል። ይህም የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ከማራዘም ባለፈ፣ የመስተንግዶ፣ የትራንስፖርት፣ የባህልና የንግድ አገልግሎቶችን በማነቃቃት ለሀገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲፈጠር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
የተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶች
በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የሀገሪቱን የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች በማስፋፋትና የመዳረሻ ብዝሃነትን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት አስመዝግበዋል። በዚህም ከታሪካዊ ቅርሶች ባሻገር የባህል፣ የተፈጥሮ፣ የኢኮ ቱሪዝምና የኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋፋት፣ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የቱሪዝም አቅም በተሻለ ሁኔታ እንድትጠቀም መንገድ ከፍተዋል።
የቱሪዝም መዳረሻዎች መስፋፋት የውጭ ጎብኚዎችን ቁጥር ከማሳደጉ ባለፈ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲጠናከር በማድረግ ዜጎች የሀገራቸውን ታሪክ፣ ባህልና ተፈጥሯዊ ጸጋዎች እንዲያውቁና እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ይህም የቱሪዝም ገቢን በማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬ ምንጭን በማስፋፋትና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚጨምረውን አስተዋጽኦ ከፍ አድርጎታል።
በተጨማሪም ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ጉልህ አበርክቶ እያስገኘ ነው። በተለይም ወጣቶችና ሴቶች በኢኮ ቱሪዝም፣ በባህል ውጤቶች ንግድና በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች በመሳተፍ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል ፈጥሯል። በመሆኑም ቱሪዝም ከመዝናኛ ዘርፍ ባሻገር የልማት፣ የሥራ ዕድልና የኢኮኖሚ ለውጥ ማስፈንጠሪያ ምሰሶ እየሆነ መጥቷል።
ማጠቃለያ
ኢትዮጵያ ጥንታዊ የታሪክ፣ የባህልና የተፈጥሮ ሃብቶቿን ከዘመናዊ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ጋር በማስተሳሰር፣ በኮሪደር ልማት፣ በተሻሻለ የአገልግሎትና በዓለም አቀፍ የማስተዋወቅ ስራዎች በቱሪዝም ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ እየጻፈች ትገኛለች። የተቀናጀው የልማት አቅጣጫ ሀገሪቱ ለዘመናት የያዘቻቸውን ዕምቅ የቱሪዝም ሀብቶች ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ጥቅም፣ የሥራ ዕድልና የሀገር ገጽታ ግንባታ ማጎልበቻ እየቀየረ ይገኛል።
ዛሬ ቱሪዝም የኢኮኖሚ አንድ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል፣ የባህልና ታሪክ መዳረሻ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ዘንድ ተመራጭ ሀገር ለማድረግ የሚያግዝ ስትራቴጂያዊ አቅም ሆኗል። ይህም ለሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ገጽታ፣ የባህል ትስስርና የዓለም አቀፍ ተሳትፎ አዲስ ዕድል ፈጥሯል።
በተለይም የዲጂታል ዘመን የቱሪዝም ዘርፉን ለማስተዋወቅ ዕድሎችን የሚያሰፋ በመሆነኑ ይህንኑ በመጠቀም፣ እንደ አይሾ ስፒድና ዲላን ፔጅ ያሉ ዓለም አቀፍ ተከታይ ያላቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የኢትዮጵያን ውብ ተፈጥሮ፣ ባህልና ታሪክ ለዓለም በማስተዋወቅ የሀገሪቱን ዓለምአቀፍ ትኩረት እያሳደጉ ናቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ቱሪዝምን ከጉብኝት ዘርፍ ባሻገር የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሀገር ገጽታ ግንባታና የዓለም አቀፍ ትስስር መሣሪያ በማድረግ ወደ አዲስ የቱሪዝም ዘመን እየተሸጋገረች ትገኛለች።
ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ፤ የኢትዮጵያ አዲሱ የብልፅግና ዘመን የኢኮኖሚ መሰሶነቱን በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል።