በክልሉ የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ለማጠናከር በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ለማጠናከር በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል
ሆሳዕና ፤ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሰላም እሴቶችን በመጠቀም የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ለማጠናከር በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው "ብዝሀነትና የሰላም እሴታችን ለዘላቂ ሰላማችን" በሚል መሪ ሀሳብ ከሀይማኖት ተቋማት መሪዎችና የባህል ሽማግሌዎች ጋር የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ አካሂዷል።
የቢሮው ምክትልና የሰላም ግንባታና ብዝሃነት አያያዝ ዘርፍ ሀላፊ አቶ እንዳለ ወልደአማኑኤል በመድረኩ እንደገለጹት፤ የክልሉን ሰላም አስጠብቆ ለማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው፡፡
ለዘመናት የዳበሩ ቱባ ዕሴቶች የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ለማጠናከርና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ለዚህም ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓትን በጥናት ላይ በተደገፈ መልኩ የማጠናከር ጨምሮ ሰላምን ጠብቀው የሚያስቀጥሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል ።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የየም ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ አባ ገብረ ሚካኤል መንግስቴ፤ የህዝቦች አብሮነት መጠናከር ለአካባቢው ፈጣን እድገት መረጋገጥ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ለዚህም አብሮነትን በሚያጠናክሩና ለዘላቂ ሰላም ግንባታው መሰረት የሚጥሉ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኙና ተግባሩን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል።
በክልሉ የተጀመሩ ትልልቅ የልማት ስራዎች እንዲሳለጡና እንዲጠናከሩ ሰላምን ማስጠበቅና አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባ ያነሱት ደግሞ የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ኡስታዝ ሼህ በኸጃ አብድልጀሊል ናቸው።
ምክር ቤቱ የክልሉን ህዝቦች አብሮነትን በማጠናከር ለጋራ ተጠቃሚነት መረጋገጥ አበክሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ሰላምን ማስጠበቅ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አይተኬ ሚና እንደሚጫወት የተናገሩት ደግሞ የሀድያ ባህል ሽማግሌ ዳኛ ብርሃኑ ጡሞሮ ናቸው።
ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም ሰላምን ጠብቆ በማስቀጠልና የህዝቦችን አብሮነት በማጎልበት የልማት ስራዎችን ለማጠናከር በሚከናወኑ ተግባራት ሚናቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።