ቀጥታ፡

የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ትልቅ ዓላማ ያለው በመሆኑ ተሳትፏችን ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2018(ኢዜአ)፦ የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ትልቅ ዓላማ ያለው በመሆኑ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (POA) ሚዲያ አመራርና ሠራተኞች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የፐልስ ኦፍ አፍሪካ (POA) ሚዲያ አመራርና ሠራተኞች ለ17ኛ ጊዜ ዛሬ ደም ለግሰዋል።

መርሐ ግብሩ በየሦስት ወሩ በቋሚነት የሚከናወነው የማኅበራዊ ኃላፊነት አካል ሲሆን፣ የዘንድሮው ደግሞ ከክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባራት ጋር ተያይዞ መከናወኑ ተገልጿል።

ደም ልገሳ በትራፊክ አደጋ፣ በወሊድ እና በተለያዩ ጉዳቶች ምክንያት ደም የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ከሞት ለማዳን እጅግ ወሳኝ መሆኑም ተመላክቷል።


 

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሕግ፣ የሥነ-ምግባርና ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ዳይሬክተርና የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ ታደለች ቦጋለ፤ የደም ልገሳው በተቋሙ ሠራተኞች በጎ ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት በየሦስት ወሩ በቋሚነት እየተከናወነ የሚገኝ ነው ብለዋል

የሚለገሰው ደም በወሊድ ወቅት ደም ለሚያስፈልጋቸው እናቶች እና በሆስፒታሎች በደም እጥረት የሚቸገሩ ወገኖችን ጤና እና ሕይወት ለመታደግ የሚያስችል በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል

የደም ልገሳው 17 ጊዜ የተደረገ ሲሆን፣ የአሁኑ ከክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ ጋር ተያይዞ መከናወኑ ልዩ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል


 

የኢዜአ እና የፒኢኤ የኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ ዮሐንስ ወንድይራድ፣ ኢዜአ መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ የማድረግ ዋና ተልዕኮውን ከመወጣት ጎን ለጎን እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ እና ደም ልገሳ ባሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

የኢዜአ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ተከታይ ደለለኝ በበኩላቸው፣ ለበርካታ ጊዜ ደም መለገሳቸውን አስታውሰው ደም መለገስ ለሌላ ሰው መትረፍ በመሆኑ እጅግ ደስተኛ ሆኜ ነው የምለግሰው ብለዋል።

በተቋሙ የፋይናንስ ባለሙያ ትግስት ብርሃኑ በደም እጥረት የሚሰቃዩ ወገኖችን የምንታደግበት በጎ ተግባር በመሆኑ ከፍተኛ የመንፈስ እርካታ ፈጥሮብኛል ብላለች።


 

ደም መለገስ ከሰብአዊ ተግባር ባለፈ የሌሎችን ሕይወት መታደግ ጭምር በመሆኑ በጎ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገረው ደግሞ የአፋን ኦሮሞ ዲጂታል ዘርፍ ጋዜጠኛ ቶሌራ ኢዶሳ ነው።

በተቋሙ የአረብኛ ሥራ ክፍል ጋዜጠኛ ቢንያም ተስፋዬ በበኩሉ የምለግሰው ደም ሰዎችን ሕይወት ስለሚታደግ በቀጣይም ይህን በጎ ተግባር አጠናክሬ እቀጥላለሁ ብሏል።


 

በኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ተንቀሳቃሽ ቡድን ነርስ የሆኑት ፍሥሐ ለወየሁ በበኩላቸው፣ በየጊዜው በወሊድ ምክንያት ለሚቸገሩ እናቶችና በተለያዩ ህመሞች የደም እጥረት የሚገጥማቸው  ወገኖችን ሕይወት ለመታደግ ደም መለገስ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል።

በተጨማሪም የደም ልገሳ ከሚሰጠው መንፈሳዊ እርካታ ባሻገር ለለጋሹም ቢሆን አዳዲስ የደም ሴሎች እንዲተኩ በማድረግ በኩል ከፍተኛ የጤና ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል።

ባለሙያው አቅም በሚፈቅደው ልክ ሰዎችን ለመርዳት ከሚደረጉ በጎ ተግባራት አንዱ ደም መለገስ በመሆኑ፣ ይህንን ባህል አድርጎ መቀጠል እንደሚገባ መክረዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም