በምዕራብ ሸዋ ዞን ጤፍን በኩታ ገጠም በማልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን ጤፍን በኩታ ገጠም በማልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ተችሏል
አምቦ፤ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ)፦በምዕራብ ሸዋ ዞን ጤፍን በኩታገጠም በማልማት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደተቻለ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ ገለፁ።
በዞኑ ኤጀርሳ ለፎ ወረዳ በመኸር አዝመራው በ4 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የጤፍ ሰብልን በኩታ ገጠም የመዝራት መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የምዕራብ ሸዋ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ በዞኑ በተያዘው የመኸር ወቅት ምርትና ምርታማነትን በመጨመር በምግብ ራስን ለመቻል የተጣለውን ግብ ለማሳካት እየተሰራ ይገኛል።
ከለውጡ ዓመታት ወዲህ ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ለመጠቀም በመቻሉ ምርትና ምርታማነትን ለተከታታይ ጊዜያት ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተረፈ አራርሳ በበኩለቸው እንዳሉት፤ በዞኑ የጤፍ ልማቱን በተሻለ መንገድ ስኬታማ ለማድረግና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየቱን እና በዚህም የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን አክለዋል።
በዞኑ በምርት ዘመኑ 84 ሺህ ሄክታር መሬት በጤፍ ዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አንስተው፣ እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ 58 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልፀዋል።
የኤጄርሳ ለፎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከበደ ለሊሳ በበኩላቸው ፤በተያዘው የመኸር ወቅት ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን በማቀድ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥም ከ12 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በጤፍ ሰብል ለማልማት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲቻልም የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በተሻለ ሁኔታ መቅረቡን ጠቁመው አርሶ አደሩ የግብርና ፓኬጆችን ሙሉ በሙሉ እንዲተገብርም ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በልማቱ እየተሳተፉ ካሉት የወረዳው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ከበደ ፊጣ እና ዲዳ ጉታ፤ ባለፉት አራት ዓመታት ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በኩታ ገጠም ጤፍ በማልማት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን አግኝተው የእርሻ ስራዎችን በወቅቱ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በተያዘው የምርት ዘመንም ጠንክረውና ተቀናጅተው በመስራት ከአንድ ሄክታር እስከ 21 ኩንታል የጤፍ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።