የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ከተፈጥሮ ሀብት ጋር ተጣጥመው እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ከተፈጥሮ ሀብት ጋር ተጣጥመው እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ለመከላከል የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር አጣጥሞ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሉን በማስመልከት የተቋሙ አመራሮችና ባለሙያዎች "75 ዓመታት ኢትዮጵያን በመንገድ ያስተሳሰረ ጉዞ" በሚል መሪ ሀሳብ የአረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።
የአስተዳደሩ የመንገድ ሀብት ማኔጅመንት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አለማየሁ አየለ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ አስተዳደሩ ባለፉት 75 ዓመታት ኢትዮጵያን በመንገድ መሰረተ ልማት እያስተሳሰረ መጥቷል ብለዋል።
የሚከናወኑ የመንገድ ግንባታዎች የተፈጥሮ አካባቢውን በማይጎዳ መልኩ እንዲገነቡ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን እንደ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና የናዳ አደጋዎችን ለመከላከል መሰረተ ልማቶችን ከተፈጥሮ ጥበቃ ጋር አጣጥሞ መስራት የጉዳት መከላከያ ስትራቴጂ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የመንገድ ግንባታዎች ተፈጥሮን በማይጎዳ መንገድ እንዲሰሩ ከመደረጉ በላይ፣ በመንገድ ኮሪደሮች ላይ ዛፎችን የመትከልና የተፈጥሮ ሀብትን የመንከባከብ ስራዎች ከዲዛይን አሰራር ጀምሮ ታሳቢ ተደርገው እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር ተጣጥመው እንዲሄዱ መደረጉን አንስተዋል።
በአስተዳደሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ብርሃኑ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ አስተዳደሩ ባለፉት 75 ዓመታት ከ180 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶችን ገንብቷል ብለዋል።
በግንባታ ሂደት የተጎዱ መሬቶች ወደነበሩበት ተፈጥሯዊ ይዘት እንዲመለሱ መደረጉንም ጨምረው ተናግረዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለአካባቢ ጥበቃ ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ጠቁመው፤ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ እንዲጸድቁ የመንከባከብ ስራ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።
በደን ሀብት አካባቢዎች የሚሰሩ መንገዶች በተፈጥሮ ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ በአቅጣጫ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በግንባታ ወቅት የሚጎዱ የተፈጥሮ አካባቢዎችን መልሶ የመተካት ሀገራዊ ግዴታውን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአካባቢ፣ ማህበራዊ፣ የስራ ቦታ ጤናና ደህንነት አስተዳደር ዳይሬክተር ኢንጂነር ነጻነት ወርቁ ናቸው።