ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ገንቢ ሚናዋን እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ገንቢ ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን ሩዋንዳዊያን መኮንኖች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ያሰለጠናቸውን 71ኛ ዙር መተማ ኮርስ ዕጩ መኮንኖችን አስመርቋል።

አካዳሚው ከኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተጨማሪ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ አፍሪካውያን ዕጩ መኮንኖችንም አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡


 

ከተመራቂዎቹ መካከል ሩዋንዳዊቷ ምክትል መቶ አለቃ ኔገና ሉሲ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአካዳሚው የንድፈ-ሐሳብና የተግባር ትምህርትና ስልጠና አግኝተዋል።

ኢትዮጵያ በኮሪያ ጦርነት፣ በሩዋንዳ እና በሌሎች አፍሪካ ሀገራት በነበራት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ደማቅ ታሪክ ማስመዝገቧን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ትምህርትና ስልጠና የላቀ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች የሚሰጥ መሆኑን በማንሳት፤ ለአፍሪካ ቀንድና ለአህጉራዊ ቀጣናዎች ሰላምና ደህንነት ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው ሩዋንዳዊ ምክትል መቶ አለቃ ፍሬሞትዋ ሂርዋ፤ በኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት መወጣት የሚያስችል የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመከላከል ለዓለም ሰላምና ደህንነት እየሰራች መሆኑን ገልጸው፤ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሀገራት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ መሰልጠናቸው ሀገሪቱ ለቀጣናዊ ሰላምና ደህንነት የምታደርገውን ትብብር ያሳያል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም