ቀጥታ፡

ወልቂጤ ከተማን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል

ወልቂጤ ፤ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ)፦ የወልቂጤ ከተማን የኮሪደር ልማት በተያዘለት ጊዜ በማጠናቀቅ ከተማዋን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።

የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በከተማዋ በሁለተኛው ዙር እየተገነባ ያለውን የ6 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡


 

በዚህም ከተማዋን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው የኮሪደር ልማቱ ፋውንቴይን ፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያ፣ የእግረኛ መንገድ ፣ የልጆች መጫወቻን ጨምሮ ፕላዛዎችን አካቶ እየተገነባ ነው ብለዋል፡፡

ከመጀመሪያው ዙር ልምድ የተወሰደበት ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት በመንገድ ዳርቻ ያሉ የንግድ ተቋማትንም በአዲስ መልክ በመገንባት የከተማዋን ገጽታ እየቀየረ ሲሆን በለሙ ቦታዎችም የጥላ ዛፎች እየተተከሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከ70 በመቶ በላይ የተጠናቀቀው የኮሪደር ልማት ከ220 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተያዘለት ሲሆን እስከ ፊታችን ነሃሴ መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሻምበል በደዊ መሃመድና አቶ ሃብታሙ እሸቱ እንደተናገሩት፤ የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገፅታ በመቀየር ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን እያደረጋት  ነው።


 

በተለይም ከዚህ ቀደም የነበረውን የመንገድ ጥበት በመቅረፍ ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ተመራጭና ተወዳዳሪ እያደረጋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በኮሪደር ልማቱ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል ሲራክ ተመስገን በሰጠው አስተያየት፤ ልማቱ ሙያዊ አቅሙን ከማሻሻልና የስራ ባህልን ከመቀየር ባለፈ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳደረገው ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም