ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል እያገዘ ነው

ጎንደር፤ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ)፦ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዜጎች መካከል የእርስ በእርስ የመረዳዳት ባህል እንዲጎለብት በማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል እያገዘ መሆኑን  የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ገለፁ።

የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ኃላፊዎችና ሰራተኞች በጎንደር ከተማ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።


 

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃሚድ ኪኒሶ በመርሐ ግብሩ እንደገለፁት፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በራስ አቅም ከመፍታት ባሻገር የእርስ በእርስ የመረዳዳት ባህልን እያሳደገ ይገኛል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የአቅመ ደካማ ዜጎች መኖሪያ ቤቶችን በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ ሰፊ ጥረት እንደሚደረግም ነው የተናገሩት።

ተቋሙ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ተክሎችን እና የደን ዛፎችን ከመትከል ባለፈ  ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍ  ማሕበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው፤ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሲካሔድ የቆየው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በዘንድሮ ዓመትም ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።


 

የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር በምግብ ራስን ለመቻል፣ የመሬት  ለምነትና የውሃ ሀብቶችን ጠብቆ ለማቆየት ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶችና የመንግስት ተቋማት ውስጥ ያሉ ክፍት ቦታዎችን በመጠቀምም ለምግብነት የሚያገለግሉ የፍራፍሬ ችግኞች እየተተከሉ መሆኑንም አንስተዋል።

እነዚህ ተክሎች ለማህበረሰቡ ጥቅም የሚሰጡና በምግብ ራስን ለመቻል የሚረዱ በመሆናቸው ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉም ማሕበረሰቡ የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው ነው ያመለከቱት።


 

በክረምቱ ወቅት እየተተገበረ ባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ለተማሪዎች ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገንና ሙሉ በሙሉ በመገንባት አበረታች ውጤት እየታየ መሆኑን ገልፀዋል።

አገልግሎቱ ለ300 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ  ድጋፍም አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም