ቀጥታ፡

በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት ውጤት ተመዝግቧል

ታርጫ ፤ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠ ትኩረት ውጤት መመዝገቡን  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን በታርጫ ከተማ እያካሄደ ነዉ።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ክንውን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳመላከቱት፤ የክልሉ ዋነኛ የኢኮኖሚ አቅም ለሆነው የግብርና ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በበጀት አመቱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ሜካናይዜሽን እና የክላስተር እርሻን በማስፋት ዘርፉን ለማዘመን የተሰራው ስራም መሻሻል ማሳየቱን ተናግረዋል። 

በመኸርና በልግ ወቅት እንዲሁም፣ በበጋ መስኖ በዋና ዋና ሰብሎች ከ801 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን ከ23 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ በስራስር፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንሰት ከ80 ሚሊዮን  ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ጠቅሰዋል።

በቡና፣ በሻይና ቅመማ ቅመም ልማትም ምርትን ለማሳደግ የተሰራው ስራ ፍሬያማ እንደነበር ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ61 ሺህ ቶን በላይ  ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።


 

ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ከሚያስችሉ ግብዓቶች መካከል አንዱ የሆነውን ምርጥ ዘር በራስ አቅም ለማባዛት በተሰጠው ትኩረትም ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።

በሌማት ትሩፋት ዘርፍ በዶሮ፣ በማር፣ በወተትና በዓሳ መንደሮችን ማደራጀትና የተደራጀቱን በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሰፊ ጥረት መደረጉንም አንስተዋል።

ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የመጠባበቂያ እህል እና መጠባባቂያ ፈንድ የማሰባሰብ ስራ በትኩረት መሰራቱንም ተናግረዋል።  

በሌላ በኩል የክልሉን የገቢ አቅም በማሳደግ የታቀዱ የልማት ግቦችን ለማሳካት በተደረገ ጥረት ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

ከስራ እድል ፈጠራ አንፃርም በበጀት ዓመቱ ለ78 ሺህ በላይ ወጣቶችን በገጠርና በከተማ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዉ፣ ለወጣቶቹ የመስሪያና መሸጫ ቦታዎችን የማመቻቸት እንዲሁም የብድር አቅርቦት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም