ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ማሳለጫና የጋራ አሸናፊነት ማብሰሪያ ነው

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ):-ሀገራዊ ምክክሩ የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ማሳለጫና የጋራ አሸናፊነት ማብሰሪያ መሆኑን የምክክር ጉባኤው ተመካካሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በማወያየት ምክክር የሚደረግባቸው ስምንት አጀንዳዎችን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በዚህም አራት ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ምክክር እያደረጉ ነው።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አሕመድ ሁሴን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ምክክሩ አንዱ የሌላውን ፍላጎት እና አተያይ በአግባቡ እንዲረዳ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ምክክሩ ዜጎች ፍላጎታቸው ማስረዳት የሌሎችን ሀሳብ መስማት የሚችሉበትን የጋራ መድረክ ፈጥሯል ብለዋል።

ጉባኤው ለሀገር ግንባታ ገንቢና ጠቃሚ ሀሳቦች የሚነሱበት በኢትዮጵያ አዲስ ባህል እና ልምምድ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዜጎች መካከል መተማመንን መፍጠር የሚያስችል አሳታፊ እና አካታች ጉባኤ በመሆኑ ለሀገረ መንግስት ግንባታ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተር አቶ መስዑድ ገበየሁ፤ የሀገራዊ ምክክር ጉባዜ ለዘመናት የቆዩ ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመምታት ትልቅ እርምጃና ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።

ኅብረቱ ከአስር በላይ ታዛቢዎችን በማሰማራት በጉባኤው የብዙሃን ማኅበረሰብ ተወካዮች በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በንቃት ሀሳብ ሲያንሸራሽሩ መታዘቡን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመላው ኢትዮጵያ የተወከሉ ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን በቋንቋቸው በነጻነት መግለጽና ማዳመጥ የሚችሉበት አስተርጓሚዎችን ማሰማራቱን ገልጸዋል።

የተመካካሪዎች ንቁ ተሳትፎ በአጀንዳዎቹ ላይ የጋራ ፖለቲካዊ መግባባት በመፍጠር ተቋማዊ መፍትሔ ለማመንጨት የጎላ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወጣት ዮሴፍ አበራ በበኩሉ፤ በምክክር ጉባኤው ተሳትፎው የተለያዩ ልምድና ተሞክሮ ማግኘቱን ገልጿል።

በምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋግጡ ሀሳቦች እየመነጩ መሆኑን በመግለጽ፤ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችል ስኬት እንደሚመዘገብ ተስፋ አለኝ ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም