በዲፕሎማሲ ዘርፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ወጣቶችን ማፍራት የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዲፕሎማሲ ዘርፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ወጣቶችን ማፍራት የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ):-በዲፕሎማሲ ዘርፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ወጣቶችን ማፍራት የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ሁለተኛ ዙር የአንድ ወር የክረምት የዲፕሎማሲ ሥልጠና (Summer Camp) የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው፣ በፍጥነት እየተለዋወጠና እየተወሳሰበ በመጣው ዓለም ውስጥ የዲፕሎማሲ ብቃትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት አስፈላጊ ነው።
በኢንስቲትዩቱ የስትራቴጂካዊ አጋርነት ዋና ዳይሬክተርና የዋና ዳይሬክተሩ ጽሕፈት ቤት ጊዜያዊ ኃላፊ ግዛቸው አስራት (ዶ/ር)፤ ሥልጠናው ወጣቶች በፍጥነት እየተሳሰረና እየተወሳሰበ በመጣው ዓለም በራስ መተማመን እንዲሳተፉ፣ ወሳኝ የትንተና አስተሳሰብ፣ የባህል ተሻጋሪ የመግባቢያ ክህሎት፣የአመራር ብቃትና የችግር ፈቺ ክህሎት እንዲያገኙ ለማብቃት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝበዋል።
ኢንስቲትዩቱ በወጣቶች ላይ በቀጣይነት ኢንቨስት በማድረግ፣በሀገራዊ፣ በቀጣናዊና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ የሚያበረክት አዲስ ትውልድ ለማፍራት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ወጣት ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች በሀገራዊ፣በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችሉ መድረኮችን የመፍጠር ሥራ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ሥልጠናው የዕውቀትና የአመራር ክህሎትን ለማጎልበት፣በመረጃ ላይ የተመሠረተ ተሳትፎን ለማበረታታትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚመጥን ትውልድ ለመገንባት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት የተካሄደው የመጀመሪያ ዙር የክረምት ሥልጠና፣ ተሳታፊዎች ሙያዊ ትስስር እንዲፈጥሩና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ስላላት ሚና ሰፊ ግንዛቤ እንዲያገኙ ዕድል መፍጠሩንም አስታውሰዋል።
በዘንድሮው ሥልጠና የፖሊሲ ውይይቶች፣ የድርድር ልምምዶች፣ ከታዋቂ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራንና የፖሊሲ አውጪዎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ከሥልጠናው ዋና ዋና ተግባራት መካከል እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
በኢንስቲትዩቱ የባለድርሻ አካላት ሥልጠናና አማካሪ አገልግሎት ጊዜያዊ ዋና ዳይሬክተር መላኩ ሙሉዓለም፤ ኢንስቲትዩቱ በጥልቅ ምርምር፣ በስትራቴጂያዊ ትንበያና የዲፕሎማሲ አቅምን በማጎልበት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማገልገል እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁለተኛው ዙር የክረምት ሥልጠና፣ ከዓለም አቀፍ ግንኙነትና ከውጭ ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ከ10 በላይ የሥልጠና ርዕሶች መካተታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ፣ ይህ ለአንድ ወር የሚቆይ ሥልጠና ወጣቶች ስለ ዲፕሎማሲ ያላቸውን ዕውቀት በተግባር የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል።
ከሥልጠናው በኋላም ወጣቶች ከኢንስቲትዩቱ ጋር በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚሳተፉባቸው ዕድሎች እንደሚኖሩ አክለዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቀጣናዊና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ያላት ሚና እየጎለበተ በመምጣቱ፣ የኢንስቲትዩቱም ኃላፊነትና ሚና እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት ሥልጠናውን የሚቀላቀሉት ሠልጣኞችም፣ የኢትዮጵያን የውጭ ፖሊሲ ስትራቴጂያዊ አስተሳሰብ በመቅረጽ ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም አካል እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል።