ቀጥታ፡

አሜሪካ አጋርነትን በማጠናከር በአፍሪካ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ናት

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ)፦አሜሪካ አጋርነትን በማጠናከር በአፍሪካ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ (AFRICOM) ጋር በመተባበር ያዘጋጀችውና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የተሳተፉበት የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 25 ቀን በሚካሄደው ሲምፖዚየም፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂንና የሎጂስቲክስ አቅምን በማሳደግ የአህጉሪቱን የጸጥታ ተግዳሮቶች በጋራ መቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት አድርጓል።

በሲምፖዚየሙ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን፣ የመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናንት ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል፣ የመከላከያ ሰራዊት ጄኔራል መኮንኖችና የአፍሪካ ሀገራት የጦር መሪዎች ታድመዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካን የፀጥታና ደኅንነት ተግዳሮቶች ለመግታት በአህጉሪቷና በዓለም አቀፍ አጋሮች መካከል ጠንካራ ትብብርን መገንባት ያስፈልጋል።

ሲምፖዚየሙም በአፍሪካና በአሜሪካ መካከል ዘላቂ አጋርነትን በመገንባት ተቋማትን ለማጠናከር፣ ወታደራዊ ትምህርትን ለማስፋፋትና ዘላቂ የመከላከያ ኢኮኖሚን ለማበረታታት እንደሚያስችል ገልጸዋል። 

አሜሪካም ለአፍሪካ ሀገራት የምታደርገውን የመከላከያ ድጋፍ በማጠናከር ዘላቂ ወታደራዊ ዝግጁነትን ለማጎልበት ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ወታደራዊ ሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን መጎልበትም የዜጎችን ሁለንተናዊ ደኅንነት በማስጠበቅ አህጉራዊ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል። 

በዚሁ መሰረትም ጠንካራ ወታደራዊ ዝግጁነትና ትብብርን በማጎልበት ሽብርተኝነትን፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ የሳይበር ጥቃትንና ግጭቶችን በጋራ መመከት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

የሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየም በመንግሥትና በወታደራዊ ተቋማት፣ በሀገራትና በመንግሥታት፣ እንዲሁም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን ትብብር እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል። 

ተሳታፊዎችም ውይይቶችን ወደ ተጨባጭ አቅም የሚቀይር ምክክር እንዲያደርጉ ጥሪ በማቅረብ፤ ሲምፖዚየሙ እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም