ቀጥታ፡

በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን  ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የልማት ፍላጎትን ለማሟላት የተጀመሩ ጥረቶች ይጠናከራሉ 

አርባምንጭ፤ ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ) ፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን  ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የልማት ፍላጎትን ለማሟላት የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር  ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2019 ዕቅድ ላይ ያተኮረ የምክክር ጉባኤ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን  ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት እየተደረገ ባለው ጥረት ውጤት እየተገኘ ነው ።

በተያዘው የ2019 በጀት አመትም የክልሉን የገቢ አቅም ለይቶ በተደራጀ ህዝባዊ ንቅናቄ የግብር እቅድን ለማሳካት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዚህም በበጀት አመቱ የታቀደውን 48 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የገቢ ዕቅድ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።

የህግና የአሠራር ስርአት በመታገዝ የገቢ አቅምን በማስፋት የክልሉን ዕድገት ዘላቂነት በማረጋገጥ የህዝቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ዓለምነሽ ደመቀ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በገቢ ራስን ለመቻል በተደረጉ ጥረቶች አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።


 

ባለፉት ዓመታት በየዓመቱ 7 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የገቢ ዕድገት መመዝገቡን ጠቅሰው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 32 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ተቋማዊ የመፈጸም አቅም በማሳደግና ብልሹ አሠራርን በማስወገድ የገቢ ስራው በዲጅታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ መሠራቱን ገልጸዋል።

በ2019 የበጀት ዓመት የክልሉን ወጪ 75 በመቶ በውስጥ አቅም ለመሸፈን የታቀደውን ግብ ለማሳካት በቅንጅት እንደሚሠራ የቢሮ ሃላፊዋ አመልክተዋል።

በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሮች የስራ ሃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም