ቀጥታ፡

የአፍሪካን የፀጥታና ደኅንነት ተግዳሮቶች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ወታደራዊ ዝግጁነትን የሚያጠናክር ጠንካራ የሎጂስቲክስና ተናባቢ የኮሚዩኒኬሽን አቅም መገንባት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካን የፀጥታና ደኅንነት ተግዳሮቶች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ወታደራዊ ዝግጁነትን የሚያጠናክር ጠንካራ የሎጂስቲክስና ተናባቢ የኮሚዩኒኬሽን አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ (AFRICOM) ጋር በመተባበር ያዘጋጀችውና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የተሳተፉበት የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 25 ቀን በሚካሄደው ሲምፖዚየም ዘመናዊ ቴክኖሎጂንና የሎጂስቲክስ አቅምን በማሳደግ የአህጉሪቱን የጸጥታ ተግዳሮቶች በጋራ መቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት አድርጓል።

በሲምፖዚየሙ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን፣ የመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናንት ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል፣ የመከላከያ ሰራዊት ጄኔራል መኮንኖችና የአፍሪካ ሀገራት የጦር መሪዎች ታድመዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ መድረኩን ለማስተናገድ መመረጧ ለአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት ያላትን ገንቢ ሚና የሚያስመሰክር ነው።

የ2026 የአፍሪካ የሎጂስቲክስና የኮሚዩኒኬሽን ሲምፖዚየም ማካሄዱም የኢትዮጵያና አሜሪካን ስትራቴጂክ አጋርነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባን የልማት ውጤቶች ከማስገንዘብ ባሻገር መዲናዋ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን በብቃት የማስተናገድ አቅም እንዳላት በተግባር የሚያረጋግጥ ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል።

የአፍሪካን የፀጥታና ደኅንነት ተግዳሮቶች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትም ወታደራዊ ዝግጁነትን የሚያጠናክር ጠንካራ የሎጂስቲክስና ተናባቢ የኮሙዩኒኬሽን አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።


 

የሲምፖዚየሙ የቴክኒካዊ ውይይቶችም አህጉራዊ ትብብርን በማጠናከር፣ ልምድና ተሞክሮ በመለዋወጥ የደኅንነት ተግዳሮቶችን መመከት የሚያስችሉ ተቋማትን ለመገንባት ወሳኝ ናቸው ብለዋል።

በትብብርና በፈጠራ ወታደራዊ ዝግጁነትን ማሳደግ፣በሰራዊቶች መካከል ያለውን ተናባቢነት ማጠናከር የሲምፖዚየሙ ዓላማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሲምፖዚየሙ ለአህጉሪቱ ሰላም፣ ደኅንነትና ዘላቂ ልማት የጋራ አቅም የሚፈጥር መሆኑን በመጠቆም፤ተሳታፊዎችም የወደፊቱን የደኅንነት ፍላጎቶች ታሳቢ ያደረገ ፍሬያማ ውይይት እንዲያካሂዱ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም