ሰራዊቱ ለሀገሩ በጀግንነት ከመቆም ባለፈ በልማት ተግባራት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው-ሜጀር ጄነራል ተስፋዬ ረጋሳ - ኢዜአ አማርኛ
ሰራዊቱ ለሀገሩ በጀግንነት ከመቆም ባለፈ በልማት ተግባራት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው-ሜጀር ጄነራል ተስፋዬ ረጋሳ
ባህርዳር፤ ሃምሌ 20/2018(ኢዜአ)፡- መከላከያ ሰራዊት ለሀገሩ ክብርና ሉአላዊነት በጀግንነት ከመቆም ባለፈ በልማትና በጎ ተግባራት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን በምስራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ ረጋሳ ገለጹ።
የምስራቅና ሰሜን ምእራብ እዞች ስታፍ አመራሮችና አባላት በባህር ዳር መኮድ ካምፕ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ከተሳተፉት መካከል የምስራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ ረጋሳ፤ ሰራዊቱ በተሰማራበት ግዳጅ ሁሉ አደራውን በላቀ ብቃትና ጀግንነት እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።
ሰራዊቱ ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላትና ከውስጥ ተላላኪ ባንዳዎች የጥፋት ተልእኮ በመጠበቅ የሀገሩን ክብርና ሉአላዊነት ማስከበሩን አንስተው በልማትና በጎ ተግባራት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው እለትም የምስራቅና የሰሜን ምእራብ እዞች አመራሮችና አባላት በጋራ በመሆን የአረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር የልማት አለኝታነታቸውን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።
ሰራዊቱ ችግኝ ሲተክል ሰላምን በማወጅ የአገር ልማትን ለማረጋገጥ፣ የለመለመ አካባቢ ለመፍጠርና የቀጣዩ ትውልድ መጻኢ እድልና ተስፋ ብሩህ መሆኑን ለማብሰር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
"ሰራዊቱ ሁል ጊዜም የሰላምና ልማት ተልእኮውን ለመወጣት ዝግጁ ነው" ያሉት ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ በቀጣይም ከሰላም ማስጠበቅ ጎን ለጎን የሚያከናወናቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሰሜን ምእራብ እዝ የደረጃ-3 ሆስፒታል አዛዥ ኮሎኔል ዶክተር ታደገ አበራ በበኩላቸው፤ ዛሬ የተተከሉት ችግኞች የአየር ንብረት ለውጥ እየደረሰ ያለውን ተጽእኖ ለመቋቋም የሚያስችሉ ናቸው።
እንደ ኮሎኔል ዶክተር ታደሰ ገለጻ ሰራዊቱ ሁልጊዜም አገርና ህዝብ የሚጥቅሙ የልማት ተግባራት ላይ ግንባር ቀደም ሚና የሚጫወት የአገር አለኝታ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሀገሪቱ ከድህነት እንድትላቀቅም በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በንቃት በመሳተፍ ሰራዊቱ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ከሰሜን ምእራብ እዝ 10 አለቃ አስናቀች በላቸው እንደገለጹት፤ የተተከሉት ችግኞች ፀድቀው ለታለመለት አላማ አንዲውሉ የእንክብካቤ ስራ ለመስራት ማቀዳቸውንም ነው የተናገሩት።
ከምስራቅ እዝ የኮማንዶ አባል ምክትል 10 አለቃ መሃመድ ታደሰ በበኩላቸው ዛሬ የተተከሉት ችግኞች ለመጭው ትውልድ ሰላሟ የተጠበቀ፣ አረንጓዴና የለመለመች አገር ለማስረከብ ያለንን ፍላጎት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ምስራቅና የሰሜን ምእራብ እዞች በተሰማሩበት የግዳጅ ቀጠና ሁሉ ባጠቃላይ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ግብ ይዘው እየሰሩ መሆኑን ከእዞቹ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።