በሀረሪ ክልል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሀረሪ ክልል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ)፦ በሀረሪ ክልል በተከናወኑ የግብርና ልማትን የማሳደግና ምርታማነትን የማሻሻል ስራዎች አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሮዛ ኡመር ገለፁ።
በተያዘው የ2019 ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ትኩረት መደረጉንም ኃላፊዋ ገልጸዋል።
ወይዘሮ ሮዛ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተከናወኑ ስራዎች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በተለይም ዓመቱን ሙሉ መልማት ከሚችሉ ምርቶች መካከል በቆሎ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው የበቆሎን ምርት በበጋና በበልግ ወቅቶች የማልማት ሥራ ሲከናወን መቆየቱን አንስተዋል።
በ2019 የበጀት አመትም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በ2018 የበጀት አመት 2 ሺህ 160 ሄክታር መሬት በቦቆሎ መሸፈን መቻሉን ገልጸው፤ በዘንድሮው የመኸር እርሻ ወደ 2 ነጥብ 378 ሺህ ሄክታር ለማሳደግ ታቅዷል ብለዋል።
በክልሉ በተጠናቀቀው የበጀት አመት ስንዴ በሄክታር ከነበረበት 32 ኩንታል በያዝነው በጀት ዓመት ወደ 33 ኩንታል ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸው 14 ሺህ 850 ኩንታል ይጠበቃል ብለዋል።
በተያዘው የበጀት አመት በመኸር እርሻ 11 ሺህ 956 ሄክታር መሬት በዘር እንደሚሸፈንና ከዚህ ውስጥም 2 ሺህ 378 ሄክታር መሬት በቦቆሎ ምርት የሚሸፈን መሆኑ ገልጸዋል።
በበልግና መኽር እርሻ የዝናብ እጥረትን ተቋቁመው በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ የማሽላ እርሻ ስራ በእጥፍ እንዲያድግና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም 4 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ልማት የተለያዩ የአትክልትና ስራስር ሰብሎች እንደሚሸፈን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ በከተማ ግብርናም 537 ሄክታር እንደሚሸፈን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ የክረምት ወቅትን ብቻ ጠብቆ ከሚሰራው የግብርና ልማት እንዲላቀቅ የግብዓት አቅርቦት፣ የመሬት ዝግጅትና የሙያተኛ አቅም ማጎልበት ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
እንዲሁም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ግብዓቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ በገጠሩ አካባቢ የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ውጤታማነት ለማሳደግ 18 የዶሮ መንደሮችን የመመስረት ስራ ይሰራል ሲሉ አብራርተዋል።
በተጨማሪም 600 ሄክታር መሬት ላይ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች እንደሚከናወኑም አብራርተዋል ።