አረንጓዴ ዐሻራ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶች እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ዐሻራ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶች እያመጣ ነው
አዲስ አበባ፣ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ):-አረንጓዴ ዐሻራ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶች እያመጣ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሀላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሀይ ጳውሎስ ገለጹ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣የቤተ መንግሥት አስተደደር እና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አመራር እና ሰራተኞች በቆቃ ቤተ መንግሥት አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሀላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሀይ ጳውሎስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ አረንጓዴ ዐሻራ የተጎዱ በርካታ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸው፤የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት እንዲሳካ መደላደል መፍጠሩን ተናግረዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ የደን ሽፋን እንዲጨምር እያደረገ ነው ያሉት ሚኒስትር ዓለምፀሀይ፤ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ዓለም አቀፋዊ ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአቮካዶ እና ቡና ችግኞች ተተክለው ለውጤት መብቃታቸውን አስታውሰው፤ይህም የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲጨምር አስችሏል ብለዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፤ አረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያን ገጽታ እየገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን በጋራ ሲሰሩ ምን ዓይነት ስኬት ሊመጣ እንደሚችል አረንጓዴ ዐሻራ ህያው ማሳያ መሆኑን ጠቁመው፤ሌሎች ሀገራትም በተሞክሮነት እየወሰዱት መሆኑ የመርሃ ግብሩን አርአያነት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማውረስ ዛሬ ችግኝ የመትከል እና መንከባከብ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የቤተ መንግሥት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ምትኩ ደሬሳ በበኩላቸው፤ በቤተ መንግሥቱ ይዞታዎች ላይ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በሰፊው እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በቆቃ ቤተ መንግሥት ባዶ የነበሩ ቦታዎች ላይ የፍራፍሬ ተክሎችን ጨምሮ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና የሚጫወቱ ተክሎች በሰፊው እየተተከለ መሆኑን አብራርተዋል።
በዛሬው ዕለትም በ12 ሄክታር መሬት ላይ የአቮካዶና ማንጎ ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው፤ ችግኞቹ የነገ ኢንቨስትመንት የገቢ ምንጭም ጭምር ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚሊዮን ኃይለሚካኤል በበኩላቸው፤ለትውልዱ የተሻለ ሀገር ለማስረከብ በተወጠነው ሀገራዊ ሁነት ላይ የበኩሌን አሻራ በማኖሬ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።
እንደ ተቋምም በአረንጓዴ ዐሻራ ያለንን ተሳትፎ አጠናክሮ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል።
ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ለውጤት ማብቃት ግባችን ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ ከብሄራዊ ቤተ መንግሥት ሙዚየም የመጡት ኮለኔል ተስፋዬ በቀለ ናቸው።