ቀጥታ፡

የአፍሪካን ደኅንነትና መረጋጋት ለማረጋገጥ ወታደራዊ ሎጂስቲክስና የኮሙኒኬሽን አቅም መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ):-የአፍሪካን ደኅንነትና መረጋጋት ለማረጋገጥ ወታደራዊ ሎጂስቲክስና የኮሙኒኬሽን አቅም መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ (AFRICOM) ጋር በመተባበር ያዘጋጀችውና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የተሳተፉበት የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 25 ቀን የሚቀጥለው ሲምፖዚየም ዘመናዊ የቴክኖሎጂና የሎጂስቲክስ አቅምን በማሳደግ የአህጉሪቱን የጸጥታ ተግዳሮቶች በጋራ መቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

በሲምፖዚየሙ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን፣ የመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አብዱራህማን እስማኤል፣ የመከላከያ ሰራዊት ጄኔራል መኮንኖችና የአፍሪካ ሀገራት የጦር መሪዎች ታድመዋል።

የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን ማንኛውንም ወታደራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን ኢንቨስትመንት ዘመናዊ የመከላከያ ቴክኖሎጂ ውጤታማነትን ለማጎልበት ጎልህ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል።

በአፍሪካ የሽብርተኝነት፣ሕገ-ወጥ ዓሣ ማጥመድ፣ ማዕድን ማውጣት፣ የሰዎችና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።

የአህጉሪቷን መሰል ተግዳሮቶች ለመቋቋም በጠንካራ ትብብር ላይ የተመሰረተ ውጤታማ የኮሙኒኬሽንና የሎጂስቲክስ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

አፍሪካ ለዓለም ደኅንነትና መረጋጋት ከፍተኛ አቅም አላት ያሉት ጄኔራል መኮንኑ፤ በቀጣይም ውስን ሃብትን በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም አዳዲስ ቴክኖሎጂና ፈጠራን ማስፋፋት ይገባል ብለዋል።


 

የሰው አልባ ተዋጊ ድሮኖች፣ ዘመናዊ የዲጂታል ኮሙኒኬሽንና ሳተላይት ቴክኖሎጂ የዓለምን የጦርነት ባህሪ በመቀየር አዲስ የጦርነት ምዕራፍ እየፈጠሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

በዚህም የአፍሪካ ሀገራት ዘመናዊ የመከላከያ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ ራሳቸውን ከዓለም የለውጥ ሁኔታና ባህሪ ጋር አብረው ማስኬድ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በሲምፖዚየሙ ላይ 26 የመከላከያና የኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ማቅረባቸውም አጋርነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ዕድል እንደሚፈጥር አመላክተዋል።

የሕክምና ድጋፍም ከሎጂስቲክስ ጋር የተሳሰረ ነው ያሉት መኮንኑ፤ ወታደሮችን በውጤታማነት ለመደገፍ የሕክምና አቅምና የአቅርቦት ስርዓት በተቀናጀ መልኩ መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሀገራት በሎጂስቲክስ፣ በኮሙኒኬሽንና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር በማጠናከር የጋራ የደኅንነት ተግዳሮቶችን በተሻለ ሁኔታ መመከት እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም