በኦሮሚያ ክልል እስካሁን በ733 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተተክለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል እስካሁን በ733 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተተክለዋል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20/2018 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን በ733 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው ጀማነህ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በተያዘው ክረምት አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የችግኝ ዓይነቶች ለመትከል ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ከታቀደው መሬት ውስጥ እስካሁን ከ733 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።
ችግኞቹ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች እየተተከሉ መሆናቸውን ተናግረው በዋናነት ለደን ሽፋን፣ ለእንስሳት መኖ፣ ቀርከሃ፣ ለውበትና ለምግብነት የሚውሉ ሁሉገብ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ችግኞቹ በመንግሥት፣ በማኅበራትና በግለሰቦች ችግኝ ጣቢያዎች የተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በልማቱም እስካሁን በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ እንደማይመታ በመጠቆም፣ ማኅበረሰቡ በተከላው ላይ በንቃት እንደተሳተፈ ሁሉ ለእንክብካቤውም በጋራ መረባረብ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።