ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአይነቱ ለየት ያለ የሎጂስቲክስና የኮሙኒዩኬሽን ሲምፖዚየም ታስተናግዳለች

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ከፍተኛ ትኩረት የሚስብ የ2026 የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየም (African Logistics and Communication Symposium) ከሃምሌ 20 እስከ 25 ቀን በአዲስ አበባ ታስተናግዳለች።

በሲምፖዚየሙ 40 ሀገራትና 26 ዋና ዋና አለም አቀፍ የኢንዱስትሪ አጋሮች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ዝግጅቱን በማስመልከት የመከላከያ የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክትሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ እና በአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) የሎጂስቲክስ ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጀነራል ፓል ፍሪክና ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ፤በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒዩኬሽን ሲምፖዚየም ኢትዮጵያ ለዚህ ታላቅ አህጉራዊ መድረክ አስተናጋጅ ሆና መመረጧ በቀጠናው ለሰላም ያበረከተችው አስተዋፅኦ፣ በመንግሥት የተመዘገበው የልማት ውጤት፣ የአዲስ አበባ ከተማ እያሳየች ያለው ፈጣን እድገት እና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ አቅሟ የፈጠረው ውጤት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሲምፖዚየሙ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የትብብር ግንኙነት የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ በአፍሪካ የመከላከያ ተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥና የጋራ ትብብር የሚያጎለብቱበት መድረክ መሆኑን አመልክተዋል።

ሎጂስቲክስና ኮሙኒዩኬሽን በማንኛውም ወታደራዊም ሆነ ሰላማዊ ተልዕኮ ስኬት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ዘርፎች መሆናቸውን የገለፁት ዳይሬክተሩ ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ፣ የተሻሉ አሠራሮችን በመቅሰም እና ለወደፊት የሚያጋጥሙ የሎጂስቲክስና የኮሙኒዩኬሽን ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ ወሳኝ አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከአጋር ሀገራት የሚገኙ ልምዶችና ዕውቀቶች ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሎጂስቲክስና የኮሙኒዩኬሽን አቅምን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ገልጸው፣ እንደዚሁም ኢትዮጵያም ያላትን ልምድ ለአጋር ሀገራት በማካፈል በአህጉራዊ ሰላምና ደህንነት ዘርፍ ያላትን አስተዋፅኦ የበለጠ እንደምታጠናክር ገልጸዋል።

የአፍሪካ የአሜሪካ ጦር ዕዝ (AFRICOM) የሎጂስቲክስ ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጀነራል ፖል ፍሊክስ በበኩላቸው፥ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የ2026 የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒዩኬሽን ሲምፖዚየምን በጋራ በማዘጋጀቷ ከፍተኛ ደስታና ክብር እንደሚሰማቸው ገልፀው፣ ለሲምፖዚየሙ መሳካት ኢትዮጵያ ያደረገችውን ዝግጅት አድንቀዋል።


 

ኮንፍረንሱ በአሜሪካና በአፍሪካ መካከል በሎጂስቲክስና በኮሙኒዩኬሽን ዘርፍ ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በቀጣዮቹ ቀናት ተሳታፊ ሀገራት የሎጂስቲክስና የኮሙኒዩኬሽን አቅሞቻቸውን በመገምገም፣ ያሉ ክፍተቶችንና ተግዳሮቶችን በጋራ በመለየት ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማፍለቅ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

ሲምፖዚየሙ በትብብር፣ በፈጠራና በጋራ ትምህርት የተሞላ ፍሬያማ ሳምንት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ በጋራ በመሥራት ጠንካራ የትስስር መረቦችን በመገንባት የሀገራትን አቅም ከፍ ማድረግና ለበለጠ ደህንነትና ብልጽግና መሠረት መጣል እንደሚቻል ተናግረዋል።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ለዚህ ዓይነት ታላቅ አህጉራዊ ጉባኤ አስተናጋጅ ሆና መመረጧ ለመከላከያና ለሀገሪቱ ትልቅ ክብር መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህ ስኬት አስተዋፅኦ ላበረከቱ የመከላከያ አመራሮች፣ የመንግሥት ተቋማት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምስጋና ማቅረባቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ያደረሰን ዘገባ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም