ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ የልጄም የነገ ተስፋ ጭምር የሚሰራበት ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ የልጄም የነገ ተስፋ ጭምር የሚሰራበት በመሆኑ ጤናዬ በፈቀደው ልክ እስከመጨረሻው ተሳትፌ አላማዬን አሳካለሁ ሲሉ በምክክር ጉባዔው ላይ ልጅ የወለዱት ሁለተኛዋ እናት ሀዳ አልመሀዲ ገልጸዋል።

እናት ሀዳ አልመሀዲ ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን ብሎም የልጆቻችንን የነገ ተስፋ ብሩህ የሚያደርግ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ምንም እንኳን ቀኔ የደረሰ ነብሰ ጡር ብሆንም ጉባኤው ላይ በመሳተፍ ሀላፊነቴን ልወጣ መጥቼ በዚህ ሂደት ላይ እያለሁ የልጅ እናት መሆን ችያለሁ ሲሉም  ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ በተመረጡት አጀንዳዎች ላይ ተጠናክሮ እየተካሄደ ሲሆን በርካታ አስገራሚ ጉዳዮችም እየታዩበት ይገኛሉ፡፡

ከዚህ ውስጥ አንዱ ደግሞ የእነ አቶ አብዱልወኪል ከማል እና ወይዘሮ ሀዳ አልመሀዲ ቤተሰብ ታሪክ ተጠቃሽ ነው፡፡

ባል አቶ አብዱልወኪል ከማል የብልጽግና ፓርቲ አባል ሲሆኑ ባለቤታቸው ወይዘሮ ሀዳ አልመሀዲ ደግሞ የተፎካካሪው የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ቤህነን ፓርቲ አመራር ናቸው፡፡


 

የግል የፖለቲካ አመለካከታቸውን በየግላቸው ይዘው የጋራ ትዳራቸውን የሚመሩት ጥንዶቹ ታዲያ ሚስት ወይዘሮ ሀዳ ፓርቲያቸውን ወክለው በምክክሩ እንዲሳተፉ በጋራ መግባባት ወስነዋል፡፡

ወይዘሮ ሀዳ አልመሀዲ በምክክሩ ሂደት ልጅ የወለዱ ሁለተኛዋ እናት ሲሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር ጋር በመሆን በኢትዮጵያዊ ባህል ወይዘሮ ሀዳን አራስ ጥሪ ይዘው መርቀዋቸዋል፡፡

ለወላዷ እናት ምክክሩ በሚካሄድበት አዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በሚገኘው ሆቴል ምቹ ማረፊያ እና አስፈላጊው እንክብካቤ እንዲደረግላቸውም ተደርጓል፡፡


 

እናት ሀዳም ታዲያ ከወሊድ ሂደቱ ጀምሮ እየተደረገልን ያለው እንክብካቤ ኢትዮጵያዊ መደጋግፍን በተግባር ያየንበት ነው ብለዋል፡፡

ምክክሩ የልጄም የነገ ተስፋ ጭምር የሚሰራበት በመሆኑ ጤናዬ በፈቀደው ልክ እስከመጨረሻው ተሳትፌ አላማዬን አሳካለሁ ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አቶ አብዱልወኪል ከማል እና ወይዘሮ ሀዳ አልመሀዲ ልጃቸው የዚህ ታላቅ ሀገራዊ ታሪካዊ ሁነት መገለጫ በመሆኑ  ስሙን "ኮሚሽን" ሲሉ መሰየማቸውንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም