ቀጥታ፡

የገጠር ሞዴል መንደር አርሶአደሩ ዘመናዊ ሕይወት እንዲመራ አስችሎታል

ቦንጋ ፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦ የገጠር ሞዴል መንደር አርሶአደሩ ዘመናዊ ሕይወት እንዲመራ አስችሎታል ሲሉ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በኮንታ ዞን አመያ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ ጨታ ቀበሌ የተገነባውን የባቾ ገጠር ሞዴል መንደር መርቀው ለተጠቃሚዎች አስረክበዋል።


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለፁት፣ ሞዴል የገጠር መንደሩ ለሰውና ለእንስሳት ምቹ መኖሪያን የሚፈጥር፣ የማር፣ የዓሳና ሌሎችም የልማት ስራዎችን ያካተተ ነው ብለዋል።


 

የገጠር ሞዴል መንደሮቹ  የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ውጤታማ በማድረግ የአርሶ አደሩን  የኢኮኖሚ አቅም  ለማሳደግ እንደሚያግዙም  ተናግረዋል።

ዛሬ የተመረቀው የባቾ ሞዴል የገጠር መንደር ይህን ለማሳካት የሚያስችል በመሆኑ  ልምዱን ማስፋት ላይ   እንደሚሰራ አንስተዋል።

የገጠር ሞዴል መንደሩ የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል  መሆኑን  የገለጹት ደግሞ የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ  ናቸው።


 

ባቾ ገጠር ሞዴል መንደር የሌማት ትሩፋትና ዘመናዊ አገልግሎቶችን ያሟላ መሆኑ የአርሶ አደሩን የአኗኗር ስርዓት የሚቀይር ነው ብለዋል።

የአመያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተመስገን ደጀኔ  በበኩላቸው፤  ትኩረት ተነፍጎት የቆየውን  የገጠሩ ማህበረሰብ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ  የገጠር ሞዴል መንደር ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።


 

የገጠር ሞዴል መንደሩ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭንና የሶላር፣ የንፁህ የመጠጥ ውሃ እና ሌሎች አገልግሎቶችንም ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል።

ከግንባታው ተጠቃሚዎች መካከል አቶ ታምሩ ተፈራ እና አቶ ተፈራ ሳካሎ፤  የገጠር ሞዴል መንደሩ  ሁሉንም አገልግሎቶች ያሟላ በመሆኑ ዘመናዊ ሕይወት መምራት ያስችለናል ብለዋል።

ይህም  የገጠሩን ማህበረሰብ  የሚያነቃቃና  የግብርና ስራዎቹን እንደሚያሳድግም  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም