ለሃገራዊ ምክክር ጉባኤ በተገኙበት የወለዱት እናቶች ጉባኤውን አጠናቀው ወደ መጡበት እስኪመለሱ ድረስ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እናደርግላቸዋለን - ኢዜአ አማርኛ
ለሃገራዊ ምክክር ጉባኤ በተገኙበት የወለዱት እናቶች ጉባኤውን አጠናቀው ወደ መጡበት እስኪመለሱ ድረስ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እናደርግላቸዋለን
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦ለሃገራዊ ምክክር ጉባኤ በተገኙበት የወለዱት ሁለቱንም አራስ እናቶች ጉባኤውን አጠናቀው ወደ መጡበት እስኪመለሱ ድረስ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እናደርግላቸዋለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፥ ሃዳ አልማህዲ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ለሃገራዊ ምክክር ከተፎካካሪ ፓርቲ ተወክላ የተጣለባትን ውክላና እና ሃላፊነት በታላቅ የሀገር ፍቅር እና የእኔነት ስሜት እየተወጣች እያለ ወንድ ልጅ በሰላም ተገላግላለች።
እኛም ወ/ሮ ሃዳን በአዲስ ዓለማቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ማረፍያ ክፍል አዘጋጅተን ለአራስ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን አሟልተን እንኳን ደስ አለሽ ብለን ጠይቀናታል ብለዋል።
ወ/ሮ ሃዳ አልማህዲ በታሪካዊው ሀገራዊ ምክክር ወቅት ላይ የወለደችውን ወንድ ልጅ ኮሚሽን ብላ ስም ማውጣታቸውንም አስታውሰዋል።
ወጣቷ የመጣችበትን ታላቅ ሀገራዊ ዓላማ ለማሳካት ከጥቂት ቀናት እረፍት በኋላ ወደ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው እንደምትመለስ መናገሯንም ጠቁመዋል።
ከንቲባ አዳነች አክለውም፥ለሃገራዊ ምክክር ጉባኤ በተገኙበት የወለዱት ሁለቱም አራስ እናቶች የመጡበትን ሃገራዊ ምክክር ጉባኤ ያለምንም ችግር አሳክተው እንዲመለሱ ለምክክሩ በቅርበት በሚመቻቸው ቦታ ማረፍያ አዘጋጅተንላቸዋል ነው ያሉት።