ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የተሻለች ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ ትልቅ ምዕራፍ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የተሻለች ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ ትልቅ ምዕራፍ ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የተሻለች ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ ትልቅ ምዕራፍ ነው ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ምክክር የሚደረግባቸውን ስምንት አጀንዳዎች በመለየት ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዋናውን ምክክር እያካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተር አቶ መስዑድ ገበየሁ እንደገለጹት፤ ለረጅም ጊዜ ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው መካሄድ መጀመሩ ትልቅ እርምጃና ስኬት ነው።
ኅብረቱ ከአስር በላይ ታዛቢዎችን በማሰማራት ባደረገው ትዝብት፤ በምክክር መድረኩ ላይ የብዙሃን ማኅበረሰብ ተወካዮች በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በንቃት ሀሳብ ሲያንሸራሽሩ መታዘቡን አብራርተዋል።
ኮሚሽኑ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ዜጎች በቋንቋቸው ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹና እንዲያዳምጡ አስተርጓሚዎችን ማዘጋጀቱ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን አክለዋል።
የተመካካሪዎች ንቁ ተሳትፎ በአጀንዳዎቹ ላይ የጋራ ፖለቲካዊ መግባባት በመፍጠር ረገድ ለተቋማዊ መፍትሔ መገኘት ከፍተኛ አጋዥ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ተመካካሪ ኡስማን መሐመድ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በየደረጃው የሚገኙ ዜጎችን ያሳተፈ በመሆኑ ከሌሎች ሀገራት የምክክር ተሞክሮ ልዩ ያደርገዋል።
የምክክሩ ሂደቱ አካታችነት በተግባር ማረጋገጡን ጠቁመው፣ ስር በሰደዱ ችግሮች ዙሪያ መግባባት ላይ ለመድረስ የተጀመረው ሂደት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አጀንዳዎቹም ከማህበረሰቡ የተሰበሰቡ በመሆናቸው፤ ከመድረኩ ሀገርን ወደ ተሻለ እድገት የሚያሸጋገር መፍትሔ ይገኛል የሚል ሙሉ እምነት እንዳላቸው አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ቀደምት ትውልዶች ያላገኙት ትልቅ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰው ትውልድን ወደፊት የሚያሸጋግር የጋራ ዓላማ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡