ሀገራዊ ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች እና የጸናች ኢትዮጵያን ለመገንባት መሰረት የሚጥል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች እና የጸናች ኢትዮጵያን ለመገንባት መሰረት የሚጥል ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ የመደማመጥና የጋራ መግባባት ባህልን በማጠናከር ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች እና የጸናች ኢትዮጵያን ለመገንባት መሰረት የሚጥል መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መጀመሩ ይታወሳል።
ያለልዩነት ሁሉንም አሳታፊ ያደረገው ይህ የምክክር መድረክ ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በመመካከር መፍተሄ ለማበጀት ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኗል።
በመሆኑም ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና ልማት የጸና መሰረት እንደሚጥልም ይጠበቃል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ተመካካሪዎች የምክክር ጉባዔው በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም እና ዕድገት ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።
ከተመካካሪዎች መካከል አቶ ሰለሞን ታፈሰ እንዳሉት፣ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈና ተመካክሮ ሀገርን በሰላም ማስቀጠል እንደሚቻል በግልጽ ያየንበት ታሪካዊ መድረክ ነው ብለዋል።
መድረኩ አለመግባባቶች ላይ በግልጽ እና በነጻነት ለመመካከር ሰፊ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ እውነተኛ መግባባት ለመፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ተመካካሪዎች የተገኙበት መድረክ በመሆኑም ይበልጥ ለመተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ተመካካሪ አቶ ነጻነት ጣሰው በበኩላቸው፥ ሀገራዊ ምክክሩ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሌሎችንም ባለድርሻዎች በሙሉ ያቀፈ በመሆኑ የሂደቱን አካታችነት በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ምክክሩ በበርካታ ጉዳዮች ላይ በሰከነ መንፈስ በመመካከር እና በመደማመጥ ሁሉም እኩል የሚሳተፍበትን መልካም አጋጣሚ መፍጠሩንም አንስተዋል።
ይህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት የመደማመጥና የጋራ መግባባት ባህልን በማጠናከር የተሻለች እና በዴሞክራሲ የጸናች ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑን አብራርተዋል።
የሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮች የሚፈቱበት እና ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙበት ታሪካዊ መድረክ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ተመካካሪ አቶ አሰፋ ወዳጆ ናቸው።
ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ለመመካከርና ሕብረብሔራዊ አንድነታቸውን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ድንቅ አጋጣሚ መሆኑን አንስተዋል።
በምክክሩ የሚደረስበት መግባባት ኢትዮጵያ ለምታልመው የሰላም ግንባታ መሰረት በመጣል፣ በአፍሪካ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የተምሳሌትነት ሚና ከፍ አድርጎ እንደሚያስቀጥል እምነታቸውን ገልጸዋል።