ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስገኙ ነው
ሰመራ፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦ ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጀመሩ የጽዳትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ውጤታማ እየሆኑ መሆናቸውን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።
ሦስተኛው ዙር ክልል አቀፍ የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ መድረክ "ፅዱ ኢትዮጵያን ለትውልድ" በሚል መሪ ሐሳብ በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ (ዶ/ር)፤ 3ኛው ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በቀጣይ ሶስት ወራት የሚተገበር መሆኑን ጠቅሰዋል።
በንቅናቄው በዋናነት የፕላስቲክ ብክለትን መከላከል፣ የአደገኛ ኬሚካሎችና ቆሻሻዎች አያያዝ፣ እንዲሁም የድምፅ ብክለትን መቀነስ ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
እነዚህ የተከናወኑ ተግባራትም ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆናቸው ጠቁመው፤ ይህንን ግብ ለማሳካት የሕግ አፈጻጸምን ማጠናከር፣ የተቋማትን ቅንጅት ማሻሻል፣ የማህበረሰብ ተሳትፎ ማሳደግ፣ የመልሶ መጠቀም ሥርዓቶችን ማጠናከር፣ እንዲሁም የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማጎልበት ዋና ትኩረቶቻችን ይሆናሉ ብለዋል።
ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያ በመንግስት ብቻ አይተገበርም ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ በየቤታችን፣ በየትምህርት ቤቶቻችን፣ በየመሥሪያ ቤቶቻችን፣ በየፋብሪካዎችና በየማህበረሰባችን በሚፈፀሙ ተደማሪ ተግባራት አቅም ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ምድራችን በአየር ንብረት ለውጥ፣ በብዝሃ ሕይወት መመናመን እና በአካባቢ ብክለት እጅጉን እየተፈተነች መሆኑን ገልፀው፤ በዚህም ምክንያት በተለይም የፕላስቲክ ብክለት በፍጥነት በመጨመሩ ምክንያት በወንዞች፣ በአፈርና በሰው ጤና ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎችና በአደገኛ ቆሻሻዎች ያልተገባ አያያዝ እንዲሁም በከተሞች እየጨመረ የመጣው የድምፅ ብክለት በሰው ጤና፣ በኢኮኖሚ እና በአካባቢ ደህንነት ላይ ከባድ ተፅዕኖ ማሳደራቸውንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በበርካታ ፖሊሲና በፕሮግራሞች የተደገፈ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም በመድረኩ አብራርተዋል።
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት እየተተገበሩ ያሉ የአረንጓዴ አሻራ፣ የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ልማት ስራዎች ሁነኛ ማሳያዎች መሆናቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ሁሉም የመንግስት ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማህበረሰብ፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የሴቶችና የወጣቶች ማህበራት እንዲሁም እያንዳንዱ ዜጋ የዚህ ሀገራዊ ንቅናቄ ባለቤት በመሆን በንቃት ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኀላፊ አቶ ኡመር ኑር፤ ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና አስተማሪ የሆኑ እርምጃዎችን በመውሰድ ለተግባራዊነቱ በየደረጃው የሚገኝ አመራር ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዶ ሃመሎ በበኩላቸው፤ በክልሉ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ የቆሻሻ አያያዝን በማሻሻል፣ የፕላስቲክ ብክለትን በመቆጣጠር፣ የብዝሃ ሕይወትን በመጠበቅና የአካባቢ ሕጎችን በማስፈጸም ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።
ለዘላቂነቱም የማኅበረሰቡን የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ በማሳደግና ከፌዴራል መንግሥት፣ ከክልሎች፣ ከልማት አጋሮች እና ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር የሚታይ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
በንቅናቄው መድረክ ላይ የአፋር ክልል ከፍተኛ የስራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።