ቀጥታ፡

በክልሉ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ ወደ ኢንቨስትመንት ለማሸጋገር የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ ነው 

ደብረ ብርሃን፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ ወደ ኢንቨስትመንት ለማሸጋገር የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) ገለጹ።

በሰሜን ሸዋ ዞን በሞረትና ጅሩ ወረዳ የሚገኙ 837 አርሶ አደሮችን ያቀፈው ማህበር “የጅሩ-አግሮ ቢዝነስ“ ኩባንያን ዛሬ መሰረተ።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) በምስረታው ወቅት እንደገለጹት፤ ኩባንያው የአርሶ አደሮችን ምርት በማቀነባበርና እሴት በመጨመር ለገበያ የሚያቀርብ ነው።

አርሶ አደሮቹ በማህበር ተደራጅተው የራሳቸውን አግሮ - ቢዝነስ ኩባንያ ማቋቋማቸው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም አርሶ አደሮቹን ከጥሬ ግብአት አቅራቢነት ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ኢንቨስተርነት በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ በበኩላቸው፤ የግብርናውን ምርታማነት በማሳደግ ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት የተሰራው ስራ ውጤታማ ሆኗል ብለዋል።


 

የተመሰረተው የቢዝነስ ኩባንያም ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮችን ምርት በጥሬው ከማቅረብ ይልቅ እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ኩባንያው የዱቄት ፋብሪካ በማቋቋምና ዱቄት በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ፣ ትራክተርና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ለማስመጣትና በሌሎች የስራ ዘርፎች በመሰማራት ዘርፉን ለማዘመን ያስችላል ብለዋል።

በምስረታው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ጀኔራል ዳይሬክተር ፍሬው ተገኘ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አርሶ አደሮቹ ትራክተርና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ዘርፉን በማዘመን ውጤታማ እየሆኑ ነው ብለዋል።


 

ኩባንያው መመስረቱም የኢንቨስትመንት ብድር በቀላሉ በማግኘት ፈጥነው የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር በከፍተኛ ዋጋ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ሀገር 50 የአግሮ ኢንዱስትሪ ኩባንያ ለመገንባት መታቀዱን ጠቁመው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በዛሬው እለት የተመሰረተው ይህ ኩባንያ አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተክለየስ በለጠ እንደገለጹት፤ የኩባንያው መመስረት የአርሶ አደሩንና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ከማሻሻሉም በላይ ፈጣን እድገት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ያበረክታል።


 

የዞኑ አስተዳደርም የተመሰረተው ኩባንያ ውጤታማ ሆኖ ለሌሎች አካባቢዎች ሞዴል እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም