ቀጥታ፡

በክልሉ የዜጎችን ጥያቄ የሚመልሱ የልማት ስራዎችን በመተግበር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል 

ቦንጋ ፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የዜጎችን ጥያቄ የሚመልሱ የልማት ስራዎችን በመተግበር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለፁ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ በ85 ሚሊዮን ብር የተገነባው የኡማ ድልድይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለፁት፣ የዜጎችን ጥያቄዎች የሚመልሱ ትልልቅ የልማት ስራዎችን በማቀድና ወደ ተግባር በመቀየር የማህበረሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው።


 

የክልሉ መንግስት ለፕሮጀክቱ ትኩረት በመስጠትና የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ማስቻሉን ተናግረዋል።

ድልድዩ አርሶአደሩ በፍራፍሬ እና በእንስሳት ልማት እንዲሁም በእርሻ ስራ ላይ በሰፊው በመሰማራት የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴው ምቹ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል፡፡

በሚከናወኑ የልማት ስራዎች የሕብረተሰቡ ተሳትፎ እያደገ የመጣ በመሆኑ ይህን አጠናክሮ በማስቀጠል የማህበረሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራትም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ በበኩላቸው፤ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ 20 የተለያየ ደረጃ ያላቸው ድልድዮች ተገንብተው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ዛሬ የተመረቀው የኡማ ድልድይ ግን በርዝማኔው የመጀመሪያ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ከሁለት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው የ84 ሜትር ርዝመት ያለው የኡማ ወንዝ ድልድይ  ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበትም ተናግረዋል።

የኡማ ወንዝ ሞልቶ በርካታ የልማት ስራዎችንና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ሲያስተጓጎል መቆየቱን የገለፁት ደግሞ የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ ናቸው።

አካባቢው ሰፊ የመልማት አቅም ያለው ነው ያሉት አቶ ታከለ፣ ድልድዩ ይህን ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳልጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ አማንን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም