ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርስቲ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት ጋር በመተባበር ያስገነባው ዘመናዊ የላቀ ላቦራቶሪ የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን የሚያሳይ ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርስቲ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት ጋር በመተባበር ያስገነባው ዘመናዊ የላቀ ላቦራቶሪ የሀገራቱ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን የሚያሳይ ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት ጋር በመተባበር ያስገነባውን የማሰልጠኛ እና የምርምር ዘመናዊ የላቀ ላብራቶሪ ስራ አስጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሀግብሩ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ፤የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርጋዴር ጀነራል ከበደ ረጋሳ፣የመከላከያ ሰራዊት ጀነራል መኮንኖች፣የተባበሩት አረብ ኢመሬትስ ተወካዮች እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።


 

ላቦራቶሪው በ20 ሺህ 850 ካሬ ሜትር መሬት ላይ የተገነባ ሲሆን በውስጡ ለስልጠና እና ምርምር የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች የተሟሉለት መሆኑ ተገልጿል።

ላቦራቶሪው በውስጡ የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የሳይበር፣ የኤሌክትሪክ ሀይል፣የአውቶሜሽን፣የኮሙኒኬሽን እና ኤሌክትሮኒክስ፣የነርሲንግ ሲሙሌሽን ላብራቶሪዎች በውስጡ ማካተቱ ተመላክቷል።

በተጨማሪም ላቦራቶሪው ዘመናዊ የሶላር ስርዓት እና ዘመናዊ መሳሪያዎች የተገጠሙለት መሆኑ ተመላክቷል።

የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በላቦራቶሪው መሰረተ ልማቱ የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ብቻውን በቂ አይደለም ብለዋል።

ይልቁንም እውቀትን ወደ ሙያዊ ብቃት፣ምርምርን ወደ ፈጠራ እንዲሁም ፈጠራን ለሀገራችን አገልግሎት ወደሚውሉ ተግባራዊ መፍትሄዎች የሚቀይር አዲስ የትምህርት የሳይንስ እና ተቋማዊ አቅም የተከፈተበት ታላቅ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የዚህ የልህቀት ምእራፍ መሰረት በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች መካከል ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት እና ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ታሪካዊ ወዳጅነት ቀደም ሲል ከነበሩት ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብሮች ባሻገር አሁን ላይ የሁለቱን ሀገራት ሀገራዊ ደህንነት፣ቴክኖሎጂያዊ ሽግግርና የተቋማትን ዘመናዊነት ወደሚያጎለብት የላቀ ምእራፍ መሸጋገሩን ጠቁመዋል።

የላቦራቶሪ ማእከሉ በቁሳቁስ ድጋፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በእውቀት ሽግግር ፣በሳይንሳዊ ምርምር እና በሀገር በቀል የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ትውልድን የሚቀርጽ መሆኑን ጠቁመዋል።

ላቦራቶሪው የመከላከያ ሰራዊቱን ሁለንተናዊ የዘመናዊነት ጉዞ የሚያፋጥን የተቋሙን የቴክኖሎጂና ምርምር መሰረት የሚያጎለብት እና የወደፊት ሀገራዊ ደህንነት በጽኑ መሰረት ላይ የሚጥል ታላቅ እርምጃ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም