የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአካባቢ ሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአካባቢ ሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 19/ 2018 (ኢዜአ):- የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአካባቢ ሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዳለው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች በብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ችግኝ በመትከል እንደ ተቋም የሚከናወነውን ዓመታዊ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ መርሐ-ግብር በይፋ ጀምረዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር የተካሄዱት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሮች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡
የሀገራችንን የተራቆተ መሬት በተለያዩ ተክሎች በማልበስ የደን ሽፋንን ማሳደግ መቻሉን ያነሱት አምባሳደር ሬድዋን፤ እየተተከሉ ያሉ ችግኞችን ውጤት መመልከት እና ማጣጣም መቻሉን አመልክተዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል አሰፋ አብዩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአካባቢ ሥነ-ምኅዳር ላይ የሚፈጸሙ ውድመቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የማኅበረሰብን ደኅንነት አደጋ ላይ እንደሚጥሉ ጠቁመዋል፡፡
በሥነ- ምኅዳር መራቆት ምክንያት የሚከሰት የዝናብ እጥረት፣ የመሬት መሸርሸርና ድርቅ ምርታማነትን በመቀነስ ሕዝቦችን ለምግብ እጥረትና ለፍልሰት በመዳረግ ብሔራዊ ደኅንነትን አደጋ ውስጥ ይከታል ብለዋል፡፡
በመሆኑም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሮች እየተከናወኑ ያሉ የተፈጥሮ እንክብካቤ እና የልማት ስራዎች እንደ አንድ ብሔራዊ ደኅንነትን የማረጋገጥ ስምሪት ተደርገው ይወሰዳሉ ብለዋል፡፡
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ሁሉንም ሠራተኞች ባሳተፈ መልኩ ችግኝ የመትከል መርሐ-ግብሩን ለማከናወን ዝግጅት አድርጓል ነው ያሉት፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተካሄዱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሮች በአጠቃላይ ከ307 ሺ በላይ የዛፍ፣ የፍራፍሬ እና የውበት ዛፍ ችግኞችን በማዘጋጀት እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ እንዲተከሉ አድርጓል፡