ቀጥታ፡

በሀዋሳ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት የከተማዋን የቱሪዝም እድገት የሚያጠናክሩ ናቸው

ሀዋሳ ፤ሐምሌ 19/2018 (ኢዜአ)፦በሀዋሳ ከተማ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማጎልበት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፉ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ገለጹ።

የሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል የእምነቱ ተከታዮች እንዲሁም በርካታ እንግዶች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል፡፡


 

በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የከተማዋ ከንቲባ ጥራቱ በየነ፤ ሀዋሳ በኮሪደርና በዘላቂ መሰረተ ልማቶች በአዲስ ምእራፍ ውስጥ ሆና የበዓሉን ታዳሚያን መቀበሏን ተናግረዋል።

በከተማዋ የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት ከተማዋን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙና ተመራጭነቷን የሚያሳድጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ምቹ የሚያደርጉ የሀይቅ ዳርቻን ጨምሮ ዘላቂ የከተማ መሰረተ ልማቶችን በፍጥነት እያከናወነ ነው ብለዋል።

በከተማዋ ለታየው ለውጥ የህዝቡ ትብብር ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባው፤ በዓመት ሁለት ጊዜ ለቅዱስ ገብርኤል የሚመጡ እንግዶችም በከተማዋ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ሃይማኖታዊ በዓላት ከእምነት ባሻገር የዜጎችን እርስ በርስ ትስስርና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባው፤ ህዝቡ በከተማው በሚኖረው ቆይታ በነጻነት እንዲንቀሳቀስና የሀዋሳን ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች እንዲጎበኝ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በበኩላቸው በዓሉ የኢትዮጵያዊያን አንድነት ጎልቶ የታየበት ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆኑ እርስ በርስ የመተጋገዝና የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር ሃይማኖታዊ ስርዓትን ማክበርና የሀገር አንድነትና ሰላምን በጋራ መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ከበዓሉ የምንማረው ፍቅርና ትእግስት ፈተናዎችን በጽኑ መሻገር እንደሚቻል ማሳያ ናቸው ያሉት ብጹዕነታቸው፤ በሀዋሳ የታየው ለውጥ የአመራሩና የህዝቡ የጋራ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

ከበዓሉ ታዳሚያን መካከል ከአዲስ አበባ የመጡት ፍሬው አበበና ወይዘሮ ማህሌት መንገሻ እንደተናገሩት የበዓሉ አከባበር እጅግ ጸጥታ የነበረበትና ያማረ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ያደረጉትን አቀባበልና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያደነቁት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ከተማዋም ከዚህ ቀደም ከነበራት ውበት በላይ በአዲስ ምእራፍ ውስጥ መሆኗን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማቷ የከተማዋን እድገት የሚያፋጥንና ተወዳዳሪነቷን የሚጨምር መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም