ቀጥታ፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክርቤት ለ2019 በጀት ዓመት ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ

አሶሳ፤ ሐምሌ 19/2018 (ኢዜአ)፡- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክርቤት በመጨረሻ ቀን የጉባዔ ውሎው ለ2019 በጀት ዓመት ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጽድቋል።

ለሁለት ቀናት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሲመክር የቆየው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክርቤት በዛሬው የመጨረሻ ቀን ውሎው ለ2019 በጀት ዓመት 25 ቢሊዮን 424 ሚሊዮን 655 ሺህ 336 ብር በጀት ነው ያጸደቀው።

የረቂቅ በጀቱን ዝርዝር ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ዚያድ አብዱላሂ እንደገለፁት በጀቱ የክልሉን ገቢ የመሰብሰብ አቅም ያገናዘበ እና ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚውል ነው ብለዋል።


 

በጀቱ ለመሠረተ ልማት እና ለትልልቅ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ትኩረት የሰጠ መሆኑን ገልፀው፥ በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላትም በጀቱን ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል።

በክልሉ የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ እየተሻሻለ በመምጣቱ ከዘንድሮ በጀት 61 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው በክልሉ የውስጥ ገቢ የሚሸፈን መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።

በረቂቅ በጀቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የምክርቤት አባላትም በጀቱን በቁጠባ እና በአግባቡ ተግባር ላይ በማዋል የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን በፍትሃዊነት መፈጸም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ምክርቤቱ በተጨማሪም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የተሻሻለ የገቢ ግብር ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅን እና የክልሉን የፋይናንስ አስተዳደርን ለማሻሻል የወጣ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በማጽደቅ ጉባኤውን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም