ባለፉት አምስት ዓመታት በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ጉልህ ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት አምስት ዓመታት በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ጉልህ ውጤቶች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦ባለፉት አምስት ዓመታት በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ ማስገኘታቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት የንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት 75 ነጥብ 59 በመቶ መድረሱን እና ከ84 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ባለፉት አምስት ዓመታት በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ለተመዘገቡት ስኬቶች አስተዋጽኦ ላበረከቱ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት አጋሮች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የእውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በዘርፉ የተመዘገቡት ውጤቶች በመንግስት አካላት፣ በክልል ተቋማትና በልማት አጋሮች የተቀናጀ ጥረት የተገኙ ናቸው።
መድረኩ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን ለማመስገን ብቻ ሳይሆን በቀጣይ የውሃና ኢነርጂ ልማት ስራዎች ላይ የተጠናከረ የትብብር አቅጣጫዎችን ለመቀየስ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
የንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትና የሳኒቴሽን አገልግሎት ሽፋን ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን ጠቁመው በከርሰ ምድር ውሃ ልማት ዘርፍ የ87 ነጥብ 5 በመቶ አፈጻጸም መመዝገቡን የሥራ ክንውን ሪፖርቱ ያመላክታል ብለዋል።
በኢነርጂ ዘርፍ ዕድገት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ትላልቅ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሀገራዊ የኤሌክትሪክ አቅምን በማሳደግ ረገድ የጎላ ሚና መጫወታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የልማት አጋሮችና አጋር ተቋማት ለዘርፉ ላደረጉት ሁለገብ ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ የተመዘገቡትን ስኬቶች አያይዞ ለማስፋትና የዜጎችን ተጠቃሚነት እያሳደጉ ለመሄድ በቀጣይም የጠበቀ ትብብር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።