የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መንግስት ጋር በመተባበር ያስገነባው ዘመናዊ የላቀ ላቦራቶሪ የሀገራቱን ዘላቂ ወዳጅነት የሚያሳይ ታሪካዊ ምልክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መንግስት ጋር በመተባበር ያስገነባው ዘመናዊ የላቀ ላቦራቶሪ የሀገራቱን ዘላቂ ወዳጅነት የሚያሳይ ታሪካዊ ምልክት ነው
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መንግስት ጋር በመተባበር ያስገነባው ዘመናዊ የላቀ ላቦራቶሪ የሀገራቱን ዘላቂ ወዳጅነት እና ስትራቴጂያዊ አጋርነትን የሚያሳይ ታሪካዊ ምልክት መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መንግስት ጋር በመተባበር ያስገነባውን የማሰልጠኛ እና የምርምር ዘመናዊ የላቀ ላቦራቶሪ ስራ አስጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሀግብሩ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣የመከላከያ ሰራዊት ጄኔራል መኮንኖች፣የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተወካዮች እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።
ላቦራቶሪው በ20 ሺህ 850 ካሬ ሜትር ላይ የተገነባ ሲሆን በውስጡ ለስልጠና እና ምርምር የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች የተሟሉለት መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ፕሮጀክቱ በእውቀት፣ በፈጠራና በሰው ኃብት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ለዘላቂ ልማትና ለብሔራዊ ደህንነት መሠረት መሆኑን የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል።
ለፕሮጀክቱ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መንግሥት ላሳየው ድጋፍና ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።
ይህም በሁለቱ ወንድማማች ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነትና የጋራ የልማት ራዕይ የሚያሳይ ተጨማሪ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
ላቦራቶሪው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የሳይበር ደህንነት፣ የመገናኛ ምህንድስና፣ የአውቶሜሽንና የቁጥጥር ሥርዓቶች፣ የኃይል ምህንድስና፣ የ3ዲ ዲዛይን፣ የፕሮቶታይፕ ልማት እና የነርሲንግ ሲሙሌሽን ዘርፎችን የሚያካትቱ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው መገልገያዎችን መያዙን ተናግረዋል።
ይህም ለከፍተኛ ትምህርት፣ ለሳይንሳዊ ምርምር፣ ለቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ ለምርት ልማት፣ ለምህንድስና መፍትሔዎችና ለቴክኖሎጂ ሽግግር የተቀናጀ መድረክ እንደሚፈጥር አንስተዋል።
በተጨማሪም ማዕከሉ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በኢንዱስትሪ፣በመንግሥት ተቋማትና በዓለም አቀፍ አጋሮች መካከል የምርምርና የፈጠራ ትብብርን የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመዋል።
የማዕከሉ ስኬት በተገጠሙ መሣሪያዎች ሳይሆን በሚያፈራቸው ብቁ ባለሙያዎች፣ በሚያመነጨው ምርምር፣ በሚፈጥረው ፈጠራና ለሀገር የሚያበረክተው ተጨባጭ አስተዋጽኦ እንደሚለካ ገልጸዋል።