ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የማሰልጠኛ እና የምርምር የላቀ ላቦራቶሪ በይፋ ስራ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች (UAE) መንግስት ጋር በመተባበር ያስገነባውን ዘመናዊ የማሰልጠኛ እና የምርምር የላቀ ላቦራቶሪ በይፋ ስራ አስጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርጋዴር ጀነራል ከበደ ረጋሳ፣ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ጀነራል መኮንኖች፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ተወካዮች እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።


 

ላቦራቶሪው በ20 ሺህ 850 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ለላቀ ስልጠና እና ምርምር የሚያስፈልጉ ዘመናዊ ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ የተሟሉለት ነው።

በውስጡ የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣የሳይበር፣የኤሌክትሪክ ኃይል፣የአውቶሜሽን፣ የኮሙኒኬሽን እና ኤሌክትሮኒክስ እንዲሁም የነርሲንግ ሲሙሌሽን ላቦራቶሪዎችን አካቷል።

ህንፃዎች በተለየ መልኩ ዘመናዊ የሶላር የኃይል ስርዓትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት ነው።


 

ማዕከሉ የተለያዩ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የመከላከያ ምርምር ዘርፎችን በአንድ ላይ የሚያገናኝ ዘመናዊ የእውቀት ማዕከል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ለዩኒቨርሲቲው ወደ ተግባራዊ ምርምርና ፈጠራ ይበልጥ ለመሸጋገር ትልቅ እምርታን የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ማዕከሉ ለመከላከያ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ አጠቃላይ የቴክኖሎጂ፣ የኢንዱስትሪ፣የጤና እና የሳይንስ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም