ተወዳዳሪ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት በስፖርት መሰረተ ልማትና ታዳጊዎች ላይ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ተወዳዳሪ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት በስፖርት መሰረተ ልማትና ታዳጊዎች ላይ መስራት ይገባል
ሀዋሳ፤ሐምሌ 19/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተወዳዳሪና ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት በስፖርት መሠረተ ልማትና ታዳጊዎች ላይ የሚሰሩ ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተጠቆመ።
እ.አ.አ. በ1957 የተመሰረተው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መስራች ከነበሩ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እግር ኳስ ዕድገት ትልቅ አሻራ አሳርፋለች።
የአፍሪካ እግር ኳስ በዓለም መድረክ የሚገባውን ቦታ እንዲይዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት የካፍ ፕሬዝዳንት የነበሩት የይድነቃቸው ተሰማ ሀገር ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ያሉባትም ናት።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እግር ኳስ ዕድገት ያኖረችውን አሻራና የቀደመ ገናና ታሪክ በማንሳት የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቧም ይታወቃል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ እና የክለቡ ተጫዋች ሁሴን ጠሃ፤ በኢትዮጵያ ተወዳዳሪ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት በመሰረተ ልማትና ታዳጊዎች ላይ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በእግር ኳሱ የላቀ ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾች እንዳሏት አንስተው ተወዳዳሪ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ዕድሎችን ለመጠቀም ብዙ ልንሰራ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የ2018ቱ የሲቢኢ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው ቡድን አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ እንደገለጸው፤ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ሌላው ዓለም የሚሰራውን መስራት መቻል አለብን ።
የስፖርት መሰረተ ልማትና የታዳጊ ስልጠና ማዕከላትን ማጠናከር፤ የምልመላ ስርዓትና የውድድር ዕድሎችን ማስፋት ቀዳሚዎች መሆናቸውን አንስቷል።
ዕምቅ ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾች የሚፈሩባቸው ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የሚደረጉ ስልጠናዎችና ውድድሮች ላይ ማተኮር እንደሚገባም አክሏል።
አሰልጣኞችን ልምድ ባላቸው ሀገራት ማስተማር፣ ወጥ የሆነ የስልጠና ማኑዋል ማዘጋጀትና ሳይንሳዊ የሆነ የምልመላ ስርዓት መዘርጋት ሌላው ሊተኮርበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አንስቷል።
መንግስት የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቡ በስፖርቱ ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ መነሳሳትን እንደሚፈጥር የጠቀሰው አሰልጣኝ ያሬድ ዕድሉን መጠቀም ይገባናል ሲል ገልጿል።
ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የመጫወት ህልም ይዞ እየሰራ ያለው የክለቡ ከ20 ዓመት በታች የግራ መስመር አጥቂ ሁሴን ጠሃ በበኩሉ፤ ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን ለመፍጠር ታዳጊዎችና የስልጠና ሜዳዎች ሊጠናከሩ ይገባል ነው ያለው።