ቀጥታ፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ133 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሯል

አምቦ ፤ ሐምሌ 19/2018 (ኢዜአ)፡-  በምዕራብ ሸዋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ 133 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

መንግስት  በሀገሪቱ የሚታየውን የወጣቶች የሥራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የክህሎት ልማት ዘርፍን በትኩረት እየሰራበት ይገኛል። 

በተለይም በክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች የወጣቶችን አቅም በማሳደግ እና በየአካባቢው የሚገኙ የኢኮኖሚ አማራጮችን በማስፋት በርካቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል።

በምዕራብ ሸዋ ዞንም በአካባቢው የሚገኙ የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለማቃለል ባለፉት የበጀት ዓመታት በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። 

ዞኑ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ምቹ የሆኑ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ያሉት ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ግብርና እና የግብርና እሴት መጨመር፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣ የአገልግሎት ዘርፍ እና ንግድ ተጠቃሽ ናቸው።

የምዕራብ ሸዋ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ የኔነሽ ምስጋና ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በ2018 በጀት ዓመት በዞኑ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ከማሳደግ ባለፈ በአገር እድገት ውስጥ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል።


 

በዚህም በዞኑ በከተማና በገጠር አካባቢዎች ለ129 ሺህ 132 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ ከ133 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።

የስራ እድሉ የተፈጠረው፣ በግብርና፣ በአገልግሎት፤ በእንጨትና ብረታ ብረት፤ የወተት ላምና የዶሮ እርባታ፣ የከብቶች ማድለብን ጨምሮ ሌሎች የሥራ  ዘርፎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ወጣቶቹ በሥራቸው ስኬታማ እንዲሆኑም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ የብድር አቅርቦት፣ የመሥሪያና የመሸጫ ቦታዎች የማመቻቸት ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በዚህ መሰረት በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብድር፣ ከ218 በላይ ሼዶችና ኮንቴይነሮች፣ 140 የሥራ ዘርፍ ክላስተሮች እንዲሁም 5 ሺህ 903 ሄክታር መሬት መቅረቡን ጠቁመዋል።

ይህንን ተግባር አጠናክሮ በማስቀጠል በአዲሱ በጀት ዓመትም በርካታ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ አዳዲስ የሥራ ዘርፎችን ለመፍጠር አቅደው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች በበኩላቸው፤ ከመንግስት የተመቻቸላቸውን የብድር ድጋፍ እና የመስሪያ ቦታ በመጠቀም፣ በትጋትና በጥንካሬ በመስራት አሁን ላይ አርአያ የሚሆን ውጤት በማስመዝገብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ወጣት ጫላ አያና፤ በቶኬ ኩታዬ ወረዳ 'የጫላና ብርቱካን የእንጨትና ብረታ ብረት ስራ' በተሰኘው ማህበር በመደራጀት ከመንግስት ባገኙት 200 ሺህ ብርና ቦታ ተግተው በመስራት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግሯል።  

በስራው የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ጠቅሶ፣ እንዲሁም 100 ሺህ ብር የተጣራ ትርፍ  ማግኘታቸውን  አክሏል።

ሌላው ወጣት አብዲ ተስፋዬ እንደገለጸው፤ በተመቻቸላቸው ዕድል በመጠቀም ባገኙት 2 ሚሊዮን ብር ካፒታል መነሻነት ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በወተት ላም እርባታ ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ነው።


 

ሥራውን በ10 ላሞች እንደጀመሩና በዚህም የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት በተሻለ ሁኔታ እየመሩ እንደሚገኙ ተናግሯል።

ከዩኒቨርሲቲ በድግሪ ከተመረቀ በኋላ ለሁለት ዓመታት ያለ ምንም ስራ ቤተሰቦቹ ላይ ጥገኛ ሆኖ መቆየቱን አስታውሶ፣ በአሁኑ ወቅት መንግስት ባመቻቸላቸው ምቹ ሁኔታን በመጠቀም ተደራጅቶ በመስራቱ ከራሱም አልፎ በኢኮኖሚው እድገት ውስጥ የራሱን ሚና ለመወጣት ማቀዱን አመልክቷል።


 

በ'ብርሃኑ ኩማላ እና ጎደኞቹ' በተሰኘው ማህበር በዶሮ እርባታ በመደራጀት በተሰጣቸው 300ሺህ ብር ብድር 800 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማስገባት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን የተናገረው ደግሞ  ወጣት ሱፋና አለሙ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም