የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚሰጠንን ማንኛውም ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ ነን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚሰጠንን ማንኛውም ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ ነን
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚሰጣቸውን ማንኛውም ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተመራቂ መኮንኖች ገለጹ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ያሰለጠናቸውን 71ኛ ዙር መተማ ኮርስ ዕጩ መኮንኖች አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጀነራል ይመር መኮንን፣ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ጌታቸው ሃብታሙ፣ ጄኔራል መኮንኖች እና የሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂ መኮንኖች በስልጠናው ያገኙትን ንድፈ ሃሳብ ከተግባር ያጣመረ ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም የሀገራቸውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከተመራቂ መኮንኖቹ መካከል የዋንጫ ተሸላሚው ምክትል መቶ አለቃ ዳዊት አዱኛ አንደገለጹት፤ በሶስት ዓመታት ወታደራዊ ስልጠና ሀገራቸውን በብቃት ማገልገል የሚያስችል ዕውቀት ቀስመዋል።
ከስልጠና ባገኙት እውቀትና ክህሎት መሰረትም ኢትዮጵያን ለማገልገል የሚሰጣቸውን ማንኛውም ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የሜዳሊያ ተሸላሚ ምክትል መቶ አለቃ ጌትነት አፈለ በበኩላቸው፤ በስልጠናው ኢትዮጵያን ሀገሬን በብቃት የማገለግልበትን ወታደራዊ ዕውቀት አግኝቻለሁ ብለዋል።
በስልጠናው ያገኙትን የዕውቀት፣ የአስተሳሰብና ክህሎት ብቃት ለሀገራቸው መልሰው ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዕድገትና ብልፅግና ጎዳና ላይ በመሆኗ የሀገሪቱን ልማት ለማደናቀፍ የሚሹ የጥፋት ኃይሎችን ተልዕኮ ለማምከን ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቆይታቸው የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ክብር ማስጠበቅ የሚያስችል ወታደራዊ ዕውቀት መቅሰማቸውን ያነሱት ደግሞ ምክትል መቶ አለቃ ኦብሳ ሰይፉ ናቸው።
የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።