ቀጥታ፡

የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የሀገረ መንግሥት ግንባታን ለማጠናከር እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችል ታሪካዊ ዕድል ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው አካታች ሀገራዊ የምክክር ሂደት የሀገረ መንግሥት ግንባታን ለማጠናከር፣ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና የሕዝቦችን አንድነት ማረጋገጥ የሚያስችል ታላቅ ዕድል መሆኑን ተመካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ምክክር የሚደረግባቸውን ስምንት አጀንዳዎች በመለየት ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዋናውን ምክክር እያካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የተጀመረው ታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ኢትዮጵያውያን በመመካከር ሀገራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መሠረት የሚጥል ነው።

በምክክር መድረኩ እየተመካከሩ የሚገኙና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ፖለቲከኞች እንዳመለከቱት፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለሰላምና ለፍትህ በርካታ ትግሎች የተደረጉ ቢሆንም የሚፈለገው ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት አልተቻሉም።

አሁን ላይ የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ግን ዜጎች በነፃነት የሚወያዩበትና በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት የሚፈጥሩበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ጎበዜ አበራ እንደገለጹት፤ ይህ እጅግ አካታችና የመላዋን ኢትዮጵያ ስብጥርና ብዝሃነት ያከበረ መድረክ፣ በሀገራችን ባልተለመደ መልኩ ችግሮችን ተነጋግሮ የመፍታት አዲስ ባህልና ሥርዓት ለመገንባት ትልቅ ተስፋ ሰንቋል።

በሂደቱ በዋና ዋና  መዋቅራዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ መግባባት ይፈጠራል ብለን እንጠብቃለን ሲሉም ገልጸዋል።


 

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ዋና ፀሀፊ ሙሉብርሃን ኃይሉ፤ በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ አማካኝነት ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት እና ተቋማት እንደሚፈጠሩና በየደረጃው ያሉ መዋቅራዊ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ሀገሪቱ ወደ ሙሉ ሰላም፣ መረጋጋት እና ዘላቂ አንድነት እንደሚያሸጋግራት አክለዋል።


 

የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፕሬዚዳንት አላምረው ይርዳው እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ቀደምት ትውልዶች ያላገኙትን ትልቅ ታሪካዊ አጋጣሚ ያመቻቸ ነው።

መላው ሕዝብ ትውልድን ወደፊት በሚያሸጋግር የጋራ ዓላማ ላይ በትብብር ሊሠራ እንደሚገባም ነው ጨምረው የገለጹት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም