ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ አርሶ አደሩን በመደገፍ ምርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ተደርጓል

ሸገር፣ ሐምሌ 18/2018 (ኢዜአ)፡-በሸገር ከተማ በተጠናቀቀው በጀት አመት አርሶ አደሩን በመደገፍ ምርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሸገር ከተማ የግብርና ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ግርማ ኃይሉ ገለጹ።

የሸገር ከተማ የ2018 በጀት ዓመት የ4ኛው ሩብ ዓመት የክትትልና አስፈጻሚ አካላት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።


 

አቶ ግርማ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ አርሶ አደሩ የሚያካሒደውን የእርሻ ስራ በሜካናይዜሽን በማገዝ እና የግብርና ግብዓቶችን በወቅቱ በማቅረብ  ስኬታማ ስራዎችን ማከናወን ተችሏል።

በ2017/18 የምርት ዘመን በከተማዋ  81 ሺህ 538 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በመስኖ ስንዴ ልማት ከ42 ሺህ 613 ሄክታር መሬት በማረስ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱንም አክለዋል።

በተያዘው የመኸር የምርት ዘመንም 95 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በተለይም የግብርና ሜካናይዜሽንን በማሳደግ ምርታማነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ነው የገለጹት።

ከዚህ በተጨማሪ የከተማው አርሶ አደር የክረምቱን ዝናብ ብቻ ከመጠበቅ ወጥቶ በሁሉም ወቅቶች ማምረት እንዲችል የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውንም  ገልፀዋል።

ለዚህም 171 ሚሊዮን ሜትር ኩብ የመስኖ ውኃ በማቅረብ 42 ሺህ 613 ሄክታር መሬት ማልማት  መቻሉን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም