የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በራስ አቅም የመልማት እድልን ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በራስ አቅም የመልማት እድልን ይፈጥራል
ጎንደር ፤ሐምሌ 18 /2018(ኢዜአ)፡-የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ገንዘብ፣ ጉልበትና እውቀት በማስተባበር በራስ አቅም የመልማት እድልን የሚፈጥር ነው ሲሉ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።
የከተማ አስተዳደሩ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወኑ ተግባራትን የሚገመግም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ መድረክ በጎንደር ከተማ አካሂዷል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኛው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ከለውጡ ዓመታት ወዲህ ትኩረት የተሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በማቃለል የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በተያዘው ክረምትም የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ ችግኝ በመትከል፣ ደም በመለገስ፣ የትምህርት ቤት ቁሳቁስ ድጋፍ በማሰባሰብ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት የመገንባትና የማደስ እና ሌሎች ተግባራት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ከ236 ሺህ በላይ ማህበረሰብን በማሳተፍ 136 ሺህ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የከተማ አስተዳደሩ አደረጃጅት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምትኩ እንዳርጌ ናቸው።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ መከናወኑ ከመንግስት ካዝና ይወጣ የነበረውን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት በማዳን የልማት ስራዎችን ለማከናወን ያስቻለ መሆኑን አስረድተዋል።
በስድስቱም ክፍለ ከተሞች እስካሁን በተካሄደው የደም ልገሳ ተግባርም ከሁለት ሺህ ዩኒት በላይ ደም ማሰባሰብ መቻሉን ጠቁመው 16 የአቅመ ደካማ ዜጎችን መኖሪያ ቤቶችን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መገንባት ተችሏል ብለዋል።
ከአራት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ለማከናወን የታቀደውን ከ60 በመቶ በላይ በበጎ ፈቃድ ስራው መፈጸም መቻሉን አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ላይም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች በለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።