ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ በ2018 በጀት ዓመት በተከናወኑት የተለያዩ የልማት ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል

ሸገር፣ ሐምሌ 18/2018 (ኢዜአ)፡-በሸገር ከተማ  ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በ2018 በጀት ዓመት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን የከተማዋ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር )ገለጹ።

የሸገር ከተማ የ2018 በጀት ዓመት የ4ኛው ሩብ ዓመት የክትትልና አስፈጻሚ አካላት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።


 

የከተማዋ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር ) ሪፖርቱንት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የከተማዋንና የማሕበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል።

በተለይም  የገቢ አቅምን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን አንስተው፣ በ2018 በጀት ዓመት 40 ነጥብ 17 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል። 

የተሰበሰበው ገቢ  መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ለማኅበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ፈጣን፣ ተወዳዳሪና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።

የተገኘው ገቢ ከአምው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ15 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

በበጀት ዓመቱ 348 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ  ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ የሕብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት ።

በከተማዋ በትምህርት ዘርፍ የተተገበሩ ኢኒሼቲቮችም በትምህርት ቤቶች ቁጥር፣ በትምህርት ዕድልና ተደራሽነት ረገድ ከፍተኛ  ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን  ነው የገለጹት። 

በዚሁ መሠረት 121 የቅድመ መደበኛ እና 15 የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ነው ያመለከቱት።

ከዚህ በተጨማሪ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብርም በ1 ሺህ 224 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተግባራዊ ሆነዋል፤በዚህም  382 ሺህ 176 ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም የተማሪዎችን መጠነ መቅረት ከማስቀረቱ ባለፈ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ማገዙን አንስተዋል።

በሸገር ከተማም የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራትም ሶስት የሚደርሱ ሆስፒታሎችን አገልግሎት ማስጀመር መቻሉ አክለዋል።

በሕብረተሰብ አቀፍ የጤና መድህን በኩልም ከአንድ  ሚሊዮን በላይ  የቤተሰብ አባላትን ማቀፍ የተቻለ ሲሆን 609 ሺህ በላይ ዜጎች   የሕክምና አገለግሎት ማግኘታቸውንም ነው የተናገሩት።

በተጠናቀቀው በበጀት ዓመት ንጹህ የመጠጥ ውሃን ተደራሽ በማድረግ 59 ነጥብ 9 በመቶ የነበረውን ሽፋን ወደ 71  በመቶ ለማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።

በዚህም 322 ሺህ በላይ የሚደርስ ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በሸገር ከተማ በ2018 በጀት ዓመት በመጀመሪያ ደረጃ እና በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች 8 ሺህ በላይ መዝገቦች እልባት አግኝተዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም