በጅማ ዞን የፍራፍሬ ምርትን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ዞን የፍራፍሬ ምርትን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተገኝቷል
ጅማ፤ሐምሌ 18/2018 (ኢዜአ) ፡-በጅማ ዞን የፍራፍሬ ምርትን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መገኘቱን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
ከዞኑ ለውጭ ገበያ የሚላክ ተጨማሪ የአቦካዶና ሙዝ ምርት የማጓጓዝ ስራ ዛሬ ተካሂዷል።
የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር እንደገለጹት በዞኑ ያለውን መሬትና የውሀ ሀብት በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
አርሶ አደሩን በመደገፍና ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንደ ቡና ሁሉ የፍራፍሬ ምርትን ለማሳደግ በተከናወነ ስራ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል ።
በተለይም ባለፉት ስድስት አመታት የተሻሻሉ የሙዝና የአቦካዶ ዝርያዎችን በማስፋፋት ምርቱን በስፋት ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
ከዞኑ በተጠናቀቀው በጀት አመት 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኪሎግራም የአቦካዶ እና ሙዝ ምርት ለገበያ መቅረቡን ጠቁመው ከዚህ ውስጥ 220 ሺህ ኪሎግራሙ ለውጭ ገበያ የቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል ።
በፍራፍሬ ልማቱ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ሆኗል ያሉት አቶ ቲጃኒ በተለይም ወጣቶች በዘርፉ ተደራጅተው ትርፋማ እየሆኑ መምጣታቸውን አመልክተዋል።
የጅማ ዞን ግብርና ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ቲጃኒ ተማም በበኩላቸው አርሶ አደሩ እየቀረበ ባለው የተሻሻለ የፍራፍሬ ዝርያ እና ሞያዊ ድጋፍ ምርቱ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል ።
የጅማ ዞን ቀርሳ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሀሰን መሀመድ በሚደረግልን ሞያዊ ድጋፍ አቦካዶን በማምረት ከ2014 ዓ. ም ጀምሮ ለዉጪ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆኛለሁ ብለዋል።